
7ኛውን የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የድንገተኛ ሕክምና ቡድኖች ዓለም አቀፍ ጉባኤ ከጥቅምት 24 እስከ 26 ቀን 2019 ዓ.ም እየተካሄደ ሲሆን በጉባኤው መክፈቻ ስነ-ስርዓት ወቅት ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ምደባ ማረጋገጫ የእውቅና ሰርተፍኬት ተሰጣት፡፡
ዶ/ር መልካሙ አብቴ የኢንስቲትዩቱ ም/ዋና ዳይሬክተር ጉባኤውን እና የምደባ ማረጋገጫ የእውቅና ሰርተፍኬት አሰጣጡን አስመልክቶ እንደገለጹት በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የድንገተኛ ቡድኖች ስብሰባ በጤና ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና በዓለም ጤና ድርጅት በጋራ በቅንጅት የተዘጋጀ መሆኑን አስታውሰው፣ ጉባኤው በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ መካሄዱ እጅግ ልዩ የሚያደርገው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባሳየችው የድንገተኛ የጤና አደጋ ዝግጁነት፣ ችግሮች ሲፈጠሩ የመከላከልና የመቆጣጠር አቅም፣ በሰው ኃይል፣ በግብዓት እና በአጠቃላይ በአሰራር ስርዓት እንዲሁም በተለያዩ አደጋዎችና ወረርሽኞች ወቅት በተደረጉ የምላሽ ስራዎች ላለፉት ሁለት ዓመታት ባሳየችው ዓለም አቀፍ መስፈርት መሰረት ተፈላጊውን ተደራሽነት አሟልታ በመገኘቷ በአስቸኳይ ሕክምና ቡድን የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ዓለም አቀፍ ምደባ ማረጋገጫ የእውቅና ሰርተፍኬት ማግኘት መቻሏን ዶ/ር መልካሙ አያይዘው አብራርተዋል፡፡
ዶ/ር መልካሙ ጨምረው እንደገለጹት ዓለም አቀፍ ምደባ ማረጋገጫ የእውቅና ሰርተፍኬት መገኘቱ ከአገር ውጪ ለሚከሰቱ የድንገተኛ ችግሮች እገዛ ለመስጠት ከፍተኛ ጥቅም ያለው መሆኑን ጠቁመው፣ የተገኘውን እውቅና ለማስቀጠልም በእስትራቴጂ ውስጥ ገብቶ እየተሰራ በመሆኑ በክልል እና በዞኖች ደረጃ የሚሰሩ ጠንካራ ስራዎችን ትኩረት በመስጠት እየተከናወኑ መሆናቸውን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡



