
ኢትዮጵያ በፓንዴሚክ ፈንድ፣ በመንግሥትና በልማት አጋሮች የ113 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ በሚተገበረው የወረርሽኝ መከላከል፣ ዝግጁነትና ምላሽ (EPPR) ፕሮጀክት ያስመዘገበችውን ውጤት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው 21ኛው የፓንዴሚክ ፈንድ የአስተዳደር ቦርድ ስብሰባ ላይ አቀረበች። የቦርዱ ስብሰባ ለሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ይቀጥላል።
የጤና ሚኒስትርና የፓንዴሚክ ፈንድ ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር መቅደስ ዳባ የመክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ዓለም አቀፍ የጤና ደህንነት፣ ቀውስ ሲከሰት ብቻ በሚደረግ ወጪ ሳይሆን በቅድመ ዝግጁነትና በዘላቂ ኢንቨስትመንት ላይ መመሥረት እንዳለበት አሳስበው፣ ኢትዮጵያ ከፓንዴሚክ ፈንድ ባገኘችው የ50 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍና በ63 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ የጋራ ፋይናንስ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቧን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።
የጤና ኤክስቴንሽን ሠራተኞችን በማንቀሳቀስ፣ የክልል የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከላትን በማሻሻልና በመግቢያ ኬላዎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተጓዦችን በመመርመር የበሽታ መከላከል አቅም መጠናከሩን አመላክተው የኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ የጤና ደንቦች (IHR) አቅም ውጤትም ከ62 በመቶ ወደ 70 በመቶ ከፍ ማለቱን ጠቁመዋል።በቀጠናው የኢቦላና የኤምፖክስ ወረርሽኝ ስጋቶች አሁንም መኖራቸውን ያስታወሱት ዶ/ር መቅደስ፣ ዓለም አቀፍ አጋሮች የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ፣ የግንባር ቀደም የጤና ባለሙያዎችን አቅም እንዲያሳድጉና ለወረርሽኞች አስቀድሞ መዘጋጀትን ቅድሚያ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ፣ ኢንስቲትዩቱ የምሥረታውን 100ኛ ዓመት በሚያከብርበት ወቅት የፓንዴሚክ ፈንድ ቦርድ አባላትን መቀበሉና የተከናወኑ ሥራዎችን በአካል እንዲገመግሙ ማድረጉ ትልቅ ክብር መሆኑን ገልጸዋል።የEPPR ፕሮጀክት የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን በፍጥነት በመለየት፣ የላቦራቶሪ አገልግሎቶችን በማሻሻልና እንደ ማርበርግ ያሉ ወረርሽኞችን በመቆጣጠር ረገድ ወሳኝ ሚና መጫወቱን አስረድተዋል።
ኢንስቲትዩቱ ወደ ሕብረተሰብ ጤና አደጋ ጊዜ አስተዳደር የልህቀት ማዕከል እየተሸጋገረ መሆኑን የጠቆሙት ዶ/ር መልካሙ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአስቸኳይ ሕክምና ቡድን በዓለም ጤና ድርጅት የዓይነት አንድ ደረጃ እውቅና ማግኘቱን በማስታወስ፣ ለተገኙ ውጤቶች አስተዋጽኦ ላደረጉ አጋሮች ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
በዚህ ፕሮጀክት የላቦራቶሪ ባለሙያዎች፣ የማኅበረሰብ ጤና ሠራተኞችና የአስቸኳይ ሕክምና ቡድን አባላት መሰልጠናቸውና በተጨማሪም አምስት ላቦራቶሪዎች ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኙ ሲሆን፣ በ719 ወረዳዎች የአደጋ ስጋት ግምገማ መካሄዱ በጉባኤው ተገልጿል።የፓንዴሚክ ፈንድ ቦርድ ፀኃፊ ፕሪያ ባሱ በኢትዮጵያ የተመዘገቡት ውጤቶች በወረርሽኝ ዝግጁነት ላይ አስቀድሞ ኢንቨስት ማድረግ ያለውን ጠቀሜታ በተግባር እንደሚያሳዩ ገልጸዋል።ኢትዮጵያ በቀጣይም የበሽታ ክትትል፣ የላቦራቶሪ አገልግሎትና የአስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ሥርዓቶችን በማጠናከር የሕብረተሰቡን ጤና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ እንደምትሠራ ያላቸውን እምነት ተገልጿል።
የመክፈቻ ጉባኤው በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ውስጥ የተሰሩ ስራዎችን ለጉባኤተኞች በማሳየት የሕብረተሰብ አደጋ ዝግጁነት አስተዳደር፣ የክስተት አስተዳደር፣ የላብራቶሪና አቅሞች፣ እንዲሁም የጥናትና ምርምር ስራዎችን በኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ እና ዶ/ር መልካሙ አብቴ እየተመራ ጎብኝቷል።






