
ግምገማው በሳምንቱ ዉስጥ የተከናወኑ የጤናና ጤና ነክ ክስተቶች ቅኝት፣ ምላሽ ላይ ያተኮረ ሲሆን በተለይም በወባ ፣ በጎርፍ አደጋ ስጋት ፣ በሥርዓተ ምግብ እና በመረጃ አያያዝ ዙሪያ የተሠሩ ሥራዎች ተገምግመዋል።
የወባ በሽታ ፣ የኬሚካል መመረዝ ሌሎች ለህብረተሰቡ የጤና ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ ጫናዎች በተዘረጋው የቅንጅት አሠራር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ መምጣታቸው ከመድረኩ ተገልጿል ፡፡
የኢንስቲትዩቱ የጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ዳይ/ ዳይሬክተር አቶ ወልደሰንበት ሸዋለም መድረኩን በመሩበት ወቅት ላይ እንደተናገሩት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚከሰተውን የወባ ጫና ለመቀነስ በተሰራዉ ጠንካራ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ በተያዘው በጀት ዓመት በሩብ ዓመቱ የወባ ጫና በ35 በመቶ መቀነሱን ገልጸዋል።
አቶ ወልደሰንበት፣የወባ ተጠርጣሪዎችን በተገቢው መለየት፣ የላብራቶሪ ተግባራትን ማጠናከርና ተገቢውን ሕክምና በወቅቱ እንዲያገኙ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የወባ ጫናን ለመቀነስ በሁሉም አካባቢዎች የተቀናጀና የተጠናከረ የክትትል ሥራ እየተሠራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ወልደሰንበት፣ ጥራት ያለው የኬሚካል ርጭት ሥራም እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ በተለያዩ ወረዳዎች ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ዝግጁነቱ መጠናከር እንደሚገባ የገለፁት ዳይሬክተሩ የሚመለከታቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ቀድሞ የግንዛቤ ሥልጠና እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።
የሥርዓተ ምግብ ጫና ያለባቸውን ወረዳዎች በመለየት ህፃናት በምግብ እጥረት እንዳይጎዱ እየተሠራ ያለው ሥራ አበረታች መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸዉ በዘርፉ የሚታዩ ውስንነቶችን በዘላቂነት ለመቅረፍ የቅንጅታዊ አሠራርን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ከታችኛው መዋቅር የሚላኩ መረጃዎችን በጥራት ማደራጀት፣ በDHIS-2 ሥልጠና መሠረት ትክክለኛ ዳታ ማስገባትና መተንተን እንዲሁም ወጥና ጥራት ያለው ሪፖርት ማዘጋጀት እንደሚገባም ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።
በግምገማው የተለዩ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የድርጊት መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ፣ ችግሮቹን ለመቅረፍ በሚያስችሉ ተግባራት ዙሪያ የጋራ መግባባት ተፈጥሮ የሳምንታዊ ግምገማው መድረክ ተጠናቋል።
በሸምሲያ አደም



