
ኢንስቲትዩቱ የአደጋ ኦፕሬሽን ማዕከል (EOC) ሳምንታዊ ስብሰባውን በማካሄድ በክልሉ የሚገኘውን ነባራዊ የህብረተሰብ ጤና ሁኔታ፣ የበሽታ ክትትልና ቅኝት፣ የወረርሽኝ ሁኔታ እንዲሁም የተወሰዱ የምላሽ እርምጃዎችን ገምግሟል።
የEOC ቡዱኑ በሳምንታዊ ስብሰባው የክልሉ ወቅታዊ የጤና ሁኔታ፣ ለህብረተሰቡ የጤና ስጋት ሊሆኑ የሚችሉ የጤናና ጤና ነክ ክስተቶች፣ የበሽታ ስርጭት፣ የተለያዩ ወረርሽኞች፣ ሪፖርቶችና የምላሽ አፈጻጸም ገምግመዋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን መድረኩን በመሩበት ወቅት፣ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችለውን የወባ ስርጭት ለመቆጣጠር በተከናወኑ ጠንካራ የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎች በሳምንቱ የወባ ጫና መቀነሱን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የወባ ተጠርጣሪዎችን በአግባቡ ለይቶ ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ለመስጠት በጤና ተቋማት የሚከናወኑ የላቦራቶሪ አገልግሎቶችን ማጠናከር ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በክልሉ የሚከሰቱ የውሻ ንክሻ ክስተቶችን በቅርበት በመከታተል የቅድመ መከላከልና የፈጣን ምላሽ ሥራዎችን ማጠናከር፣ ከሚመለከታቸው የእንስሳትና የግብርና አካላት ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚገባም ተገልጿል።
ከእብድ ዉሻ ንክሻ ጋር ተያይዞ የክትባት አሰጣጥንና የህብረተሰቡን ግንዛቤ የማሳደግ ሥራዎችም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አቅጣጫ ተቀምጧል።
የሥርዓተ-ምግብ ጫና ያለባቸውን አካባቢዎች በመለየት ህፃናት በምግብ እጥረት እንዳይጎዱ በቅንጅት መሥራት፣ ሌሎች ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ጫና ለመቀነስ የልየታና የክትትል ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ በስብሰባው ተነስቷል።
በመድረኩ በሳምንቱ ውስጥ የተከናወኑ ተግባራትና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ተገምግመው፣ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሠራር ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ አቅጣጫ በማስቀመጥ ውይይቱ ተጠናቋል።



