Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

የኢትዮጵያ 16ኛው የወባ ጥናትና ምርምር ኔትወርክ(Ethiopian Malaria Research Network: EMRN) ሳይንቲፋክ ሲምፖዚየም በድሬዳዋ ከተማ በድሬደዋ ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ።

CERPHI

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጤና ሚኒስቴር፣ ከድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ እና ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 16ኛው የኢትዮጵያ የወባ ጥናትና ምርምር ኔትወርክ (EMRN) ሳይንሳዊ ሲምፖዚየም በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በድምቀት ተካሂዷል።

“በአገር ውስጥ ሀብት ማሰባሰብን በማካተት እና በአዲስ ሳይንሳዊ ፈጠራዎችን በማጠናከር የወባ ቁጥጥርንና ማጥፋትን ማጠናከር እና ማሻሻል” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው በዚህ መድረክ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዘርፉ ተመራማሪዎችና የአጋር አካላት ተወካዮች ተገኝተው በአገሪቱ የወባ ማጥፊያ ስልቶች ላይ ጥልቅ ውይይት አድርገዋል።

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ የጥናትና ምርምር ሲምፖዚየሙን ሲከፍቱ እንደተናገሩት ፣ ኢትዮጵያ በ2030 ወባን ከአገር ለማጥፋት በያዘችው ስትራቴጂካዊ እቅድ ውስጥ የሳይንሳዊ ምርምር ሚና ምትክ የሌለው መሆኑን ጠቅሰው ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአየር ንብረት ለውጥ እና በተለያዩ ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች በአለም አቀፍ ደረጃ የወባ ስርጭት በተወሰነ ደረጃ ማድግ የታየ መሆኑን እና ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የወባ ስጋት ነፃ ባለመሆንዋ ሁለም ባለድርሻ አካላት ከኢትዮጵያ የወባ ጥናትና ምርምር ኔትወርክ (EMRN) በትብብር በመስራት የወባ ቁጥጥርና ማጥፋት ፕሮግራም የፈለገዉን መረጃ ማመንጨትና ምክረ-ሐሳብ ማቅረብ እንደሚገባ ገልጸዋል::

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱት በምርምርና ቴክኖሎጂ ላይ በማተኮር ትክክለኛ የሕብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ስርዓት በመተግበር፣ የበሽታ ልየታን ማጠናከር፣ የመድኃኒት ብግርነትን መከታተል እና የትንኞችን ጠባይ ማጥናት ላይ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም የአገር ውስጥ ሀብትን በማሰባሰብ ላይ ትኩረት በመስጠት፣ በተለያዩ የሀገራችን ወረዳዎች የተከሰተውን የወባ ግርሸትን መቆጣጠርና 4ኛው የወባ ጠቋ ሚ ጥናት በማጠናቀቅ ላይ መሆናችን ትላልቅ ውጤቶች እየተመገቡ መሆናቸዉን አስረድተዋል።

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ጌታቸው ቶሌራ በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩ በሕብረተሰብ ጤና ዙሪያ ምርምሮችን ማድረግና መረጃ ማመንጨት ዋና ተግባሩ እንደሆነ ገልጸው መንግስት ለሳይንሳዊ ምርም ነፃነት ያለውን እምነት፣ ግልጽ ከሆነው የፖሊሲ አቅጣጫ ጋር ተዳምሮ፣ ምርምሮች እንዲበለጽጉና የጤና ስርአቱን በቀጥታ እንዲደግፉ የሚያስችል ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥሯል ብለዋል። በወባ ዙሪያም የተሰሩ ጥናቶች እና ሳይንሳዊ ግኝቶች በቀጥታ ወደ ተግባር ተተርጉመው የሕብረተሰብ ጤና ሊያሻሽሉ እንደሚገባ ገልጸው፣ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለዚህ ያለው ቁርጠኝነት አስረድተዋል:: የኢትዮጵያ የወባ ምርምር ኔትወርክ (EMRN) በወባ ዙሪያ ለሚያደርገው አስተዋጽዎም ኢንስቲትዩቱ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል::

በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ዶ/ር ሕይወት ሰለሞን በበኩላቸው፣ ጤና ሚ/ር ወባን ለመከላከል፣ለመቆጣጠርና ለማጥፋት እያከናወናቸው ያሉትን አገራዊ ስራዎችን አብራርተዋል። በአሁኑ ወቅት ከብዙ ሚሊዮን በላይ ዘመናዊ አጎበሮች እየተከፋፈሉ መሆኑንና በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ ከፍተኛ ተጋላጭ ወረዳዎች ውስጥ ለሕፃናት የወባ ክትባት መሰጠት መጀመሩን ጠቁመዋል። ይህ የክትባት መርሃ-ግብር ወደ ፊት በምርምር መታገዘና በሂደትም ውጤታማነቱ የሚገመገም መሆኑን እንዳለባቸዉ ስራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ኡባህ አደም ተሳታፊዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት፣ ዩኒቨርሲቲው ለሳይንስ መድረኮችና ለሕብረተሰብ ተኮር ምርምሮች ትልቅ ዋጋ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ጽጌረዳ ክፍሌ በበኩላቸው፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደር ደረጃ የሚሰሩ ወባን የመከላክል ስራዎች በተመራማሪዎችና በጤና ባለሙያዎች ቅንጅት ሊደገፉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በጤና ሚ/ር የወባ እና ቬክተር ወለድ በሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ደስክ ኃላፊ የሆኑት አቶ ጉዲሳ አሰፋ ወባ ወቅታዊ ሁኔታዎችና ሚ/ሩ ሊሰራበት እያቀደ ያለዉን የወባ መከላከል መቆጣጠርና ብሎም ማጥፋትን በተመለከተ ረቂቅ ስትራቴጂና እቅድ ለተሳታፊዎች በስፋት ለዉይት መነሻ እንዲሆንያቀረቡ ሲሆን በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የወባ እና ትኩረት የሚሹ ሀሩራማ በሽታዎች ምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ገረመው ጣሰው ወቅታዊ የወባ ምርምር ስራን (ማለትም Malaria Operational Research Updates) በተመለከተ ለተሳታፊዎች ዝርዝር ማብራሪያ አቅርበዋል።

የምርምር ግኝቶች በተጨባጭ በኅብረተሰቡ ውስጥ እንዴት ወደ ተግባር እየተቀየሩ እንደሆነ፣ የአልጋ አጎበር ስርጭትና የኬሚካል ረጭት ውጤታማነት፣ እንዲሁም የመድኃኒት መላመድ (Resistance) ስጋቶችን ለመከላከል እየተከናወኑ ያሉ የጥናት ማሻሻያዎችን የያሰሱት ዶ/ር ገረመው እነዚህ ወቅታዊ የምርምር ውጤቶች ውሳኔ ሰጪዎች በመረጃ ላይ የተመሠረተ ሳይንሳዊ አቅጣጫ እንዲከተሉ የሚረዱ መሆኑንም አስገንዝበዋል። እንደ አስረጂነት በወባ ማገርሸት ዙሪያ በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንሰቲትዩት በጥናትና ምርምር ተመስርተዉ ለጤና ሚ/ር የቀረበዉ የኢቪደንስ ቢሪፍ በአገሪቱ ተከስተዉ የነበረዉን የወባ ማገርሸተን መቀልበስ እንደተቻለ በሰፊዉ ለተሳታፍዎች አስረድተዋል፡፡ የምርምር ውጤቶቹም ለቀጣይ የፖሊሲ አቅጣጫዎች እንደ ግብዓት እንደሚያገለግሉ በማስረዳት የኢትዮጵያ የወባ ጥናትና ምርምር ኔትወርክ(Ethiopian Malaria Research Network: EMRN) ምክረ ሀሳብ በመስጠት ለተግባራዊነቱ ያለዉ ሚና ከፍተኛ እንደሚሆን አስረድተዋል።

በመቀጠል በሁለቱም ቀናት በሁለት የተከፈሉ የአውደ ጥናት ውይይቶች ከዩኒቨርሲቲ፣ ከባለድርሻ ከካላት፣ ከኢንስቲትዩቱ እና ጤና ሚኒስቴር የተውጣጡ ምሁራኖች፣ የዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎችና የፕሮግራም መሪዎች ተሳትፈዋል። ሲምፖዚየሙ በሁለት ቀናት ቆይታው ወባን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ብሎም ለማጥፋት ኢትዮጵያ ከምንጊዜዉም የበለጠ መዘጋጀት እንዳለባትና የአንድ ጤና መርህ ማዕከል ያደረጉ ስታረቴጅም መታሰብ እንደለበትና ያስችላሉ የተባሉ ሳይንሳዊ ጥናቶች የቀረቡ ሲሆን፤ በቀረቡት ጥናቶች ላይም ሰፊ የፓናል ውይይቶችና ምክክሮች ተካሂደውባቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *