
ወራቤ፣ ሚያዚያ 24/2018 (ስልጤ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን)
የለውጡ መንግስት ባለፉት ዓመታት ትልልቅ ውጤቶችን ማስመዝገብና ትላልቅ ድሎችን ማጎናጸፍ መቻሉን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ ገለጹ።
በላንፉሮ ወረዳ በመንግስት ወጪና በአጋር አካላት እገዛ የተከናወኑ ልዩ ልዩ የልማት ፕሮጀክቶች በተመረቁበት መርሃ ግብር ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ወ/ሮ ፋጤ ያለፉት የለውጥ ዓመታት እንደ ሀገር እንዲሁም በክልልና በዞን ደረጃ በሁሉም ዘርፎች ስኬታማና ውጤታማ እንደነበሩ አብራርተዋል።
በሀገር ደረጃ ታውጆ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ስራው የከተሞችን ገጽታ በመቀየርና ከተሞችን ኑሮ ምቹ በማድረግ በኩል ውጤታማ እንደነበር ወ/ሮ ፋጤ ተናግረዋል።
በሌላም በኩል በሁሉም ሴክተሮችና ዘርፎች አገልግሎቶችን በማዘመንና በማሻሻል ዜጎች ፈጣንና ውጤታማ አገልግሎት እንዲያገኙ በስፋት መሰራቱን ወ/ሮ ፋጤ ገልጸዋል።
በገጠር በምግብ ራስን ለመቻል አዳዲስ ኢንሼቲቮች ተቀርጸው ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውንና የቁጠባ ብድር አገልግሎቶች በማስፋፋት የህዝቡን የኢኮኖሚ አማራጭ ለማስፋት በትኩረት መሰራቱን ተናግረዋል።
በተያያዘም በከተማና በገጠር ውጤት ማምጣት የቻለ የኢኮኖሚ ሪፎርም መተግበሩንና በፖለቲካ ረገድ ኢትዮጵያ የሁሉም የማድረግ ስራዎች በቁርጠኝነት መፈጸማቸውን ክብርት አፈ ጉባኤዋ አብራርተዋል።
ተቋማት በነጻነት እንዲወስኑ በመደረጉ እንደ ምርጫ ቦርድና የፍትህ ተቋማት ያሉ ሴክተሮች አርዓያነት ያለው ተግባር እያከናወኑ መሆኑንም ወ/ሮ ፋጤ ጨምረው ገልጸዋል።
በሌላም በኩል ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በመጨረስ ላይ የተሻለ ታሪክ መመዝገቡን አንስተዋል።
መንግስት የህዝብን ተጠቃሚነት በላቀ ሁኔታ ማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎችን በውጤታማነት ማከናወኑ ህዝባዊ አመኔታ እንዲኖረው ማስቻሉንና በዚህም ህዝብ በመንግስት የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች በንቃት እየተሳተፈና ውጤት እያስገኘ መሆኑንም አስረድተዋል።
የተጀመሩ ስራዎች ወደላቀ ምዕራፍ እንዲሻገሩ የህዝቡ ቅንጅታዊ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ወ/ሮ ፋጤ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ፣ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ሀላፊና የገጠር ክላስተር አስተባባሪ አቶ ኡስማን ሱሩር፣ የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ፣ የስልጤ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ መህዲያ ቡሴር፣ የስልጤ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ሀላፊና የዞኑ ዋና የመንግስት ተጠሪ ወ/ሮ ነዒማ ሙኒር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን፣ የስልጤ ዞን አስተባባሪ አካላት እና ሌሎች የክልል፣ የዞን፣ የላንፉሮ ወረዳና የጦራ ከተማ የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም ልዩ ልዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።



