Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

የክትባት ፕሮግራም እና በክትባት የምንከላከላቸው በሽታዎች ቅኝትና ምላሽ ላይ ያተኮረ ግምገማ ተጀመረ

CERPHI

በኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና በጤና ሚኒስቴር አዘጋጅነት የክትባት ፕሮግራም እና በክትባት የምንከላከላቸው በሽታዎች ቅኝትና ምላሽ ላይ ያተኮረ የዘጠኝ ወር የጋራ አፈፃፀም ግምግማ መድረክ መካሄድ ጀመረ።

የግምገማ መድረኩ ሲጀመር የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ ከአርባ አመታት በላይ ጠንካራ የክትባት ፕሮግራም እንደነበራት አስታውሰው፤ በግዜው ስድስት የክትባት አይነቶች ፕሮግራሙ የተጀመረ ሲሆን አሁን ላይ ከ60 በላይ በሚሆኑ የክትባት አይነቶች በፕሮግራሙ እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።

በነዚህ የክትባት አይነቶች ማህበረሰቡን ከሞት መታደግ መቻሉንና በተለይ በልጆች ላይ በአጣዳፊ ተቅማጥ ምክንያት የሚከሰተውን ሞት በክትባት አማካኝነት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።

በፖሊዮ ምክንያት የሚሞቱ ህፃናት ቁጥር መቀነስ መቻሉንም ተናግረው፤ በፔንታ የክትባት ሽፋን ማደግ ጋር ተያይዞ በህፃናቶች ላይ የሚከሰተውን ሞት በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ መቻሉን ዶ/ር ደረጄ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ፣ በላብራቶሪ እና በምርምር ስራዎች ላይ አተኩሮ እየሰራ እንደሚገኝ የገለፁት ዶክተር ደረጄ፤ በተመሳሳይ ከክትባት ጋር በተገናኘ በበላይነት የመምራትና የመቆጣጠር ስራዎችን በትጋት እያከናወነ እንደሚገኝና በዚህም የሀገር ኩራት መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ በህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ምላሽ፣ በላባራቶሪ አቅም ግንባት፣ በምርምርና፣ በብሔራዊ ጤና ዳታ ቅመራና አሁን ላይ ደግሞ በአንድ ጤና ላይ ያሉ ስራዎችን እየመራና እያስተባበረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ኢንስቲትዩቱ በተለይ ጠንካራ የድንገተኛ ህብረተሰብ ጤና አደጋ ስረአት እየገነባ መሆኑንና በዚህም የልህቀት ማእከል ሆኖ መውጣቱንና ይህም በሀገሪቱ ለሚከሰቱ ድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ፈጣን ምላሽ ለመስጠትና ለመቆጣጠር የሚያስችል አቅም መገንባቱን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት ሰባት አመታት በምስራቅ አፍሪካ ኮቪድ 19ኝን ጨምሮ የተለያዩ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎችና ወረርሽኞች ሀገራትን አጋጥሟቸው እንደነበር ተናግረው፤ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን በነዚህ ችግሮች ላይ ኢንስቲትዩቱ ምላሽ መስጠቱን ጠቁመዋል።

የፖሊዮ ወረርሽኝም በዚህ ቀጠና የጤና ስጋት እየሆነ መምጣቱን ዶክተር መሳይ ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከዋይልድ ፖሊዮ ነፃ መሆኗንና ለዚህም ከአለም ጤና ደረጃ ማረጋገጫ ማግኘቷን ገልፀዋል።

ከፖሊዮ በተጨማሪ በኢትዮጵያ የወባ፣ ኩፍኝ፣ፈንጣጣ፣ ኮሌራ እና ማርበርግ ወረርሽኞችም ተከስተው እንደነበረ አስታውሰው፤ እነዚህ ወረርሽኞች በመንግስትና አጋር አካላት የተቀናጀ ትብብር መቆጣጠር መቻሉን አስረድተዋል።

ዶ/ር መሳይ አያይዘውም ይህ የዘጠኝ ወር አፈፃፀም ግምገማ መድረክ ባለፉት አመታት በክትባት ፕሮግራም እና በክትባት የምንከላከላቸው በሽታዎች ቅኝትና ምላሽ ዙሪያ የተገኙ ስኬቶችን ለማየት፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለመለየትና በቀጣይ መሻሻል በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ለመፈለግ ጥሩ አጋጣሚ እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከክልል ጤና ቢሮዎች፣ ከክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶች እና ከሌሎች አጋር ደርጅቶች እና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የማይበገር የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ስርዓትን ለመገንባት ብሎም ብሄራዊ የጤና ደህንነትን ለማረጋገጥ ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል ብለዋል።

በዚህ ረገድ ኢንስቲትዩቱ አመርቂ ዉጤቶችንም እያስመዘገበ መሆኑን ጠቁመዋል። ከነዚህ ውስጥ መከላከል በምንችላቸው በሽታዎች እንደ ፖሊዮ፤ ኩፍኝ እና ሌሎችም በሽታዎች የቅኝትና የአሰሳ ተግባራትን የማከናወን፤ የላቦረቶሪ አቅምን የማገንባት እና ምርመራዎችን እዚሁ ሀገር ውስጥ የማካሄድ፤ የላቦረቶሪ ዉጤቶችን መሠረት ባደረገ መልኩ በተለያዩ ጊዜያት ለተከሰቱ ወረርሽኞች ፈጣን ምላሽ የመስጠት በተለይም የተቀናጁ የክትባት ዘመቻዎችን ወረርሽኝ በተከሰተባቸዉ እና አጎራባች በሆኑ አከባቢዎች የማካሄድ እንዲሁም የክትትል እና የግምገማ ተግባራት ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ይህ የዘጠኝ ወር የጋራ አፈፃፀም ግምገማ ዛሬን ጨምሮ ለተከታታይ ለሁለት ቀናት እንደሚካሄድ ይጠበቃል። በዚህ የአፈፃፀም ግምገማ መድረክ ላይ የጤና ሚኒስቴር: የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት : የክልል ጤና ቢሮ እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሀላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም የአጋር አካላት ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ::

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *