
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሆሳዕና ቅርንጫፍ ላቦራቶሪ አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል እና ምቹ የስራ ሁኔታ ለመፍጠር የተደረገለትን እድሳት ጉብኝት እንዲሁም ከሠራተኞች ጋር ውይይት አድርገዋል ።
የሥራ ኃላፊዎቹ ተቋሙ ያለበትን ደረጃ ምልከታ አድርገው አቅጣጫም አስቀምጠዋል።
የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዱልዋሪስ ጀማል በዚህ ወቅት እንዳሉት፦ በጤናው ዘርፍ የሚታይና ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት በመደመር መንግስት ዕሳቤ ተቋማትን ለሠራተኞች ሳቢና ምቹ ማድረግ ይገባል።
በዚህም በተቋሙ መሟላት ያለባቸውን ጉዳዮች በሂደት ለመፍታት እንደሚሰራ ተናግረዋል ዋና ዳይሬክተሩ።
ለሥራ ውጤታማነት ከባለሙያዎች የተነሱ ጥያቄዎችን እንደ ግብአት ወስደን በእቅድ እንሰራለን ነው ያሉት አቶ አብዱልዋሪስ።
የተቋሙ ባለሙያዎች ተግባሮችን በባለቤትነት በመከወን ሕብረተሰቡ ከጤናው ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል በላቀ ተነሳሽነት እንዲሰሩ አሳስበዋል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ለገሰ ጴጥሮስ በበኩላቸው በተቋሙ የሚሰጡ አገልግሎቶች ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንዲሆን ብሎም የአገልግሎት ጥራቱን ለማስጠበቅ የድጋፍና ክትትል ሥራዎች ይጠናከራሉ ብለዋል።



