
አቶ ሳሙኤል ዳርጌ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የሩብ አመቱ የጤና ልማት ስራዎች አፈጻጸም ፣ የ100 ቀናት እቅድ እንዲሁም አገራዊ የጤና ጉባኤ ዝግጅት ግምገማ መድረክ በወራቤ ከተማ አካሄደ ፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በመድረኩ ማጠቃለያ እንደገለጹት በክልሉ ፍትሃዊ ፣ ጥራት ያለው እና ተደራሽ የሆነ የጤና አገልግሎት እንዲረጋገጥ የተጀመረው ስራ ማጠናከር እንደሚገባ ገልጸዋል ፡፡
በክልሉ በጊዜው የሚሰራው የጤና ልማት ስራ የጤና ስርዓት ግንባታ የሚያጠናክር መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል ያሉት አቶ ሳሙኤል ለመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ ስራችን እንዲሁም የማህበረሰብ ተሳትፎን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል ፡፡
የጤና ተቋማት የቦርድ ውይይት የተለዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መቅረፋቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባ አስታውቀዋል ፡፡
በክልሉ ግንባታቸው ተጠናቆ ግብዓት የተሟላላቸው የጤና ጣቢያ የኦፕሬሽን መስጫዎችን አገልግሎት ማስጀመር ሌላው ትኩረት መሆኑን ጠቅሰዋል ፡፡
ለእናቶች እና ህጻናት ጥራት ያለው ህክምና ፣ ጥራት ያለው የክትባት አገልግሎቶች ላይ ተጨማሪ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባ ገልጸው በክልሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን አስቀድሞ መከላከል የሚያስችሉ ስራዎች ትኩረት እንዲሰጥም አሳስበዋል፡፡
በክልሉ አዳዲስ እና እየተተገበሩ የሚገኙ የጤና ኢንሼቲፎችን በተሻለ ማሳካት ለጤናው ዘርፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያስገኘ በመሆኑ ማጠናከር እንደሚገባው ጠቁመዋል ፡፡
28ኛው አገራቀፍ የጤና ጉባኤ በስኬት ለማካሄድ በየደረጃው እየተካሄደ የሚገኘው አስፈላጊ ቅድመ ተገናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል ፡፡
በመጨረሻም የጤናው ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል በየደረጃው ብልሹ አሰራሮችን ለይቶ ለመፍታት ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል ፡፡
በመድረኩ የቢሮ ምክትል ኃላፊዎች ፣ የማኔጅመንት አባላት ፣ የዞን እና ልዩ ወረዳ ጤና ኃላፊዎች እና የልማት እቅድ አስተባባሪዎች ተገኝተዋል ፡፡



