
እንስትቲዩቱ ለህብረተሰቡ የጤና ስጋት ሊሆኑ በሚችሉ የጤናና ጤና ነክ ክስተቶች ቅኝትና ምላሽ ተግባራት ዙሪያ ሳምንታዊ ግምገማ አካሂዷል።
የእንስትቲዩቱ ጤናና ጤና ነክ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ከለላዉ አቻምየለህ የሳምንቱን ሪፖርት ሲያቀርቡ በክልሉ የወባ በሽታን ለመከላከል በየደረጃው በተሰሩ ስራዎች በሳምንቱ 8 በመቶ የወባ ጫና መቀነሱን ጠቁመዋል
የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን እንደተናገሩት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚፈጠረዉን የወባ በሽታ ለመከላከል ጠንካራ የክትትል እና የቁጥጥር ስራዎች በልዩ ትኩረት በመሰራቱ የወባ ጫና መቀነሱን ገልፀዋል ።
ለህብረተሰቡ የወባ በሽታ የመከላከያ መንገዶችን በማስተማር እና ህመሙ ሲከሰት ፈጥኖ ወደ ህክምና ተቋሞ በመሄድ ህክምና እንዲያገኙ የማድረግ ስራ ላይ ተከታታይነት ያለዉ የግንዛቤ ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑ አቶ ማሙሽ አስረድተዋል
የወባ በሽታን በዘላቂነት ለመገታት በክልሉ ለሚገኙ ሁሉም መዋቅሮች የአጎበር ስርጭት ቢደረግም ከአጠቃቀሙ ጋር ተያይዞ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለዉን ክፍተት ለመሙላት አስተማሪ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መስጠት ይገባል ።
በክልሉ የዲጅታላይዜሽን ተግባርን ጨምሮ ጠንካራ የፌም ስርዓት በመዘርጋቱ የሚታይ ዉጤት እየተመዘገበ ስለመሆኑ የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ በቀጣይም ተግባሩ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም አመላክተዋል ።
የስርዓተ ምግብ ጫና ያለባቸው አከባቢዎችን የልየታ ስራ ላይ ማተኮር ተገቢ ነዉ ያሉት አቶ ማሙሽ በምግብ እጥረት የተጎዱ ህፃናት የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ በልዩ ትኩረት መሰራት ያስፈልጋልም ብለዋል።
አቶ ማሙሽ አክለዉም የኤች አይቪ ኤድስ በሽታ የሚያስከትለውን የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዲሁም ስነልቦናዊ ጫናን ለመቀነስ በቫይረሱ አዲስ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር በጊዜ መከታተልና መቆጣጠር እንደሚገባ አስገንዝበዋል ።
ወቅቱን የጠበቀ መረጃን በጥራት በማደራጀት በመተንተን እና በተገቢው በመያዝ ጥቅም ላይ የማዋል ባህልን ማሳደግ እንደሚገባ አቶ ማሙሽ ጠቁመዋል ።
የእንስትቲዩቱ ምክ/ዋና ዳይሬክት አቶ ለገሰ ጴጥሮስ በበኩላቸዉ ለኬሚካል መመረዝ የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች ተለይተዉ ክልላዊ ወርኪንግ ጉሩፕ በማቋቋም እና አስተማሪ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በመፍጠር ከችግሩ ፈጥነዉ እንዲወጡ ማድረግ እንደሚገባ አንስተዋል
በመድረኩ በሳምንቱ ውስጥ የተከናወኑ ተግባራትና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንዲሁም በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በሸምሲያ አደም


