
ሆሳዕና፣ሚያዚያ 12/2018 በስልጤ ዞን ዳሎቻ ወረዳ ከ74 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተመርቀዋል
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ መንግስት ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ እየሰጠ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር ለዘመናት የሀገሪቱን ስም ካጎደፈው ድህነትና ኋላቀርነት በመላቀቅ አሁን ላይ መድላድል ተፈጥሯል ብለዋል።
የተመረቁ የልማት ፕሮጀክቶች የህዝብን ተጠቃሚነት ወደ አንድ ከፍታ ከፍ የሚያደርጉ የልማት ስራዎች ናቸው ብለዋል።
በየደረጃው የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ውጤታማ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በማድረግ ረገድ የሁሉም ኃላፊነት ነው ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ እንዳሉት ህብረተሰቡን በማስተባበር ከመንግስት አቅም ጋር በማስተሳሰር በርካታ ውጤታማ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች ማከናወን ተችሏል፡፡
በዛሬው ዕለት ለምረቃ የበቁ የልማት ፕሮጀክቶች መንግስት በየደረጃው ያሉ የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት አንዱ ማሳያ ብለውታል፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በበኩላቸው የስልጤ ዞን በጤናው ዘርፍ ህዝብን በማስተባበር በጤናው ዘርፍ ያከናወናቸው ተግባራት እንደ ሀገርም በአርአያነት እንዲጠቀስ አስችሎታል ብለዋል፡፡
በተለይ ዞኑ የጤና ተቋማትን ከመገንባት ባለፈ በህክምና ቁሳቁስና የሰው ሀይል በማደራጀት በኩል ረጅም ርቀት ተጉዘዋል በዚህም አበረታች ውጤቶች አስመዝግቧል ሲሉ መናገራቸውን ከዞኑ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል ።





