Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

የሆሳዕና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በዲፕሎማና በድግሪ መርሀ ግብር ያሰለጠናቸውን 202 ተማሪዎች በተለያዩ የጤና መስክ አስመረቀ

CERPHI

የሆሳዕና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የ2018 ዓ/ም የተማሪዎችን የምረቃ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች በደማቅ ሁኔታ አክብሯል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና የሆሳዕና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የቦርድ ሰብሳቢ የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ማሙሽ ሁሴን በመረሀ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት የጤና ባለሙያዎች ለጤና ሥርዓቱ ዋና ድልድይ በመሆን የጤና አገልግሎቶችን ከጤና ተቋማት ወደ ማህበረሰቡ ማድረስ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በተለይም በቤት፣ በመንደርና በማህበረሰብ ውስጥ ህዝብን በማስተማር፣ በመከላከልና በማሳወቅ፣ በሽታ ከመከሰቱ በፊት ህይወትን የሚያድን የመከላከያ ሥራ ላይ በትኩረት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ ማሙሽ አክለውም፣ የጤና ባለሙያዎች ለለዉጥ የሚመሩ፣ለህዝብ የሚቆሙና ለተሻለ የጤና ስርዓት የሚተጉ መሆን እንደሚገባቸው ጠቁመዉ ከወላጆችና ከቤተሰቦቻቸው፣ ከመምህራኖቻቸውና ከሌሎች አጋዥ አካላት ያገኙትን ድጋፍ ወደ ተግባር በመቀየር እንዲሁም የተማሩትን እውቀት ለሰው ልጅ ጥቅም ላይ ማዋል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የኮሌጁ ዋና ዲን አቶ ኤልያስ ቲራጎ በበኩላቸው፣ በዛሬው ዕለት በዲግሪ መርሃ ግብር 132 እና በዲፕሎማ ፕሮግራም 70 ተማሪዎችን፣ በአጠቃላይ 202 ተማሪዎችን ማስመረቃቸውን ገልጸዋል።

የኮሌጁ ምክትል ዲንና የመማር ማስተማር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ድንቁ ዳንኤል እንደገለጹት፣ ኮሌጁ ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ በሰርተፍኬት፣ በ10+3፣ በደረጃ 4 እና በዲፕሎማ ፕሮግራሞች ለ29 ጊዜ ፣ በድግሪ መርሀ ግብር ደግሞ ለ3ኛ ጊዜ ተማሪዎችን አስመርቋል።

የዛሬውን ምረቃ ለየት የሚያደርገው ኮሌጁ በጄኔሪክ ዲግሪ መርሃ ግብር በፋርማሲ ሙያ ተማሪዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛ ቁጥር ማስመረቁ መሆኑን አቶ ድንቁ ጠቁመዋል። ከአጠቃላይ ተመራቂዎች ውስጥም 74.3 በመቶ የሚሆኑት ሴት ተማሪዎች መሆናቸውን አንስተዋል

በመርሃ ግብሩ ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በአፕ ግሬድ ጤና ኤክስቴንሽን፣ በሚድዋይፈሪ፣ በሜዲካል ላብራቶሪ ቴክኖሎጂ እና በፋርማሲ ፕሮግራሞች ተማሪዎችን አስመርቋል።

ተማሪ ሚልኪያስ አመዕኖ 3.96 የሆነ ውጤት በማስመዝገብ ከኮሌጁ አንደኛ ደረጃን ይዞ የተመረቀ ሲሆን በተማረበት የሙያ መስክ በትጋትና በጥብቅ የሙያ ስነ-ምግባር ህብረተሰቡን ለማገልገል ቁርጠኛ መሆኑን ገልጿል።

ሌላኛዋ የማዕረግ ተመራቂ ወ/ሪት መቅደስ ጳዉሎስ 3.91 ውጤት በማስመዝገብ በከፍተኛ ዉጤት የተመረቀች ሲሆን በቀጣይም ያስተማራትን ማህበረሰብ በቅንነትና በትጋት ለማገልገል መዘጋጀቷን ገልጻለች።

የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ማሙሽ ሁሴን በመጨረሻም ለተመራቂዎቹ የዛሬ ስኬታችሁ የብዙ ታላላቅ ስኬቶች መጀመሪያ ይሁን“ በማለት፣ በሙያቸው እንዲበለጽጉ፣ ለህዝባቸውና ለሀገራቸው ትልቅ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የስራ አቅጣጫ እና መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የኮሌጁ ምክትል ዲኖች፣ የኮሌጁ የማኔጅመንት እና አካዳሚክ ኮሚሽን ፣ መምህራን፣ የተመራቂዎች ቤተሰቦችና የተጋበዙ እንግዶች ተሳትፈዋል።

ለሁሉም ተመራቂዎች እንኳን ደስ አላችሁ::

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *