Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸሙን ገመገመ::

CERPHI

የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) የ2018 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ስትራቴጂካዊ እና ኦፕሬሽናል ዕቅድ አፈጻጸምን የክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሀላፊዎች እና የኢንስቲትዩቱ አመራሮች በተገኙበት የሚገመግም የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ ከተማ አካሄደ።

የግምገማ መድረኩ ዋና ዓላማ በሕብረተሰብ ጤና አደጋ ቁጥጥር፣ በላቦራቶሪ አቅም ግንባታና አገልግሎት በጥናትና ምርምር ፣ በብሔራዊ የጤና መረጃ ዙሪያ እንዲሁም በአለም አቀፍ ጤና ደንብና የአንድ ጤና በተመለከተ በዓመቱ የተሰሩ ስራዎችን በመገምገም የተገኙ ውጤታማ ስራዎችን ለማስቀጠል ብሎም የታዩ ክፍተቶችን በመለየት የቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ነው::

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኃይሉ መድረኩን ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር፣ ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመበት ዓላማ አንፃር በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን፣ በጥናትና ምርምር፣ የሕብረተሰቡን ጤንነት ከአደጋ በመጠበቅ በኩል፣ የክልል ጤና ቢሮዎችን፣ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቶችን አቅም በመገንባት፣ የጤና መረጃዎችን በማሰባሰብ ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ እና በአገር አቀፍ ደረጃ የላብራቶሪ አቅምን ከፍ በማድረጉ በኩል ኢንስቲትዩቱ ከፍተኛውን ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን አብራርተዋል ::

ዋና ዳይሬክተር አክለዉም፣ ተቋሙ ከቀበሌ እስከ ፌዴራል ደረጃ ያለውን የጤና ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን በከፍተኛ ትጋት እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በተለይም ባለፉት ዘጠኝ ወራት በሀገሪቱ የታዩ የጤና ስጋቶችንና ወረርሽኞችን ለመቆጣጠር የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንደነበሩ ጠቁመዋል። ከስኬቶቹ መካከል በሀገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየውን የኤም-ፖክስ (M-pox) በሽታ አስቀድሞ በመለየትና የላቦራቶሪ ማረጋገጫ በመስጠት ረገድ የተከናወነው ሥራ ይጠቀሳል።

ከዚህም በተጨማሪ የላቦራቶሪ ቴክኖሎጂን ከማዘመን ባለፈ፣ ተንቀሳቃሽ የላቦራቶሪ አገልግሎቶችን (Mobile Labs) በመጠቀም በሩቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ማኅበረሰቦችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል።

የማርበርግ ቫይረስ ስጋት በነበረበት ወቅትም ኢንስቲትዩቱ አስቀድሞ የቅኝትና የላቦራቶሪ ዝግጁነት በማድረጉ በሽታውን በፍጥነት ለመለየት የሚያስችል አቅም መገንባቱ ተገልጿል።

ዶ/ር መሳይ አክለውም፣ ኢንስቲትዩቱ የመጀመሪያውን የጤና ልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ አጠናቆ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ለመሸጋገር ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ይህም በቀጣይ አምስት ዓመታት የሚከናወኑ የጤና ጥበቃ ሥራዎችን በሳይንሳዊ መንገድ ለመምራት እንደሚያግዝ ተመልክቷል።

ከሚያዝያ 8- 9 /2018 ድረስ በተካሄደዉ በዚህ የዘጠኝ ወራት የስራ አፈፃፀም የግምገማ መድረክ ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ኢንስቲትዩቱ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ ከሕብረተሰብ ጤና አደጋ ዝግጁነትና ቁጥጥር አንፃር ፣ ከላብራቶሪ አቅም ግንባታ፣ ከጥናትና ምርምርስራ ውጤቶች ፣ ከብሔራዊ የጤና መረጃ አንፃር እንዲሁም ሌሎችም በተቋሙ የተመዘገቡ ውጤቶች በሪፖርት ቀርበው በጥልቀት እየተገመገሙ ሲሆን፤ የተመዘገቡ ውጤቶችን እና የታዩ ክፍተቶችን በመለየት በቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል::

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *