
ከመላው አገሪቱ የተውጣጡ የመንግስት ተቋማት፣ አጋሮች እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት 5ኛው የኢትዮጵያ የስነ-ሕዝብ እና የጤና ጥናት (EDHS) የመጀመሪያ ደረጃ የውጤት ስርጭት አውደ ጥናት ተካሂዷል።
በአውደ ጥናቱ ላይ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ከዳሰሳ ጥናቱ የሚመነጨው መረጃ ለብሔራዊ የጤና እቅድ ቁልፍ ግብዓት ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
ለኢትዮጵያ የስታቲስቲክስ አገልግሎቶት፣ ለልማት አጋሮች እና ለዳሰሳ ጥናቱ ቡድን ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና ያቀረቡት ሚኒስትሯ መንግስት አስተማማኝ እና ከፍተኛ ጥራት ያለው መረጃ ለማረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የስታቲስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር በከር ሻሌ ጥናቱን እንደ አገራዊ ስኬት ገልጸው፣ ይህም የኢትዮጵያን አሁናዊ የጤና ሁኔታ ግልጽ ምስል ይሰጣል ብለዋል። EDHS ለዘላቂ አመራር እና ለመልካም አስተዳደር መሠረት መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው፤ በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ አሰጣጥን እንደሚደግፍ አስረድተዋል።
የሴቶችና የማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ እንዳሉት ከጥናቱ የተገኙት ቁልፍ አመልካቾች አወንታዊ ጣልቃ ገብነቶችን እና ዘላቂ የማህበራዊ ፕሮግራሞችን እቅድ ለማውጣት ይረዳሉ። የጥናቱ ውጤት ይፋ መደረጉ መረጃው ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ መሆኑን ያረጋግጣል ብለዋል።
ጥናቱ ወሳኝ የመረጃ ምንጭ መሆኑን የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዶ/ር ፍጹም አሰፋ ገልፀው፤ ፖሊሲዎች በተረጋገጠ መረጃ ላይ መመስረታቸውን ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል።
ጥናቱ በዋናነት በጨቅላ ህፃናትና እናቶች ጤና ላይ አመላካች የሆኑ የወሊድ ምጣኔና የቤተሰብ እቅድ አጠቃቀም፣ ስለክትባት አወሳሰድ፣ እናቶች ከወሊድ በፊትና በኋላ የሚደረግላቸው የጤና እንክብካቤ፣ ኤች አይ ቪ ስርጭት፣ የህፃናት መቀንጨርና አመጋገብን የሚያሳዩ አመላካቾች እንደሚገኙበት በገለፃ የቀረበ ሲሆነ የጥናቱ ግኝቶች የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶ/ር ፍጹም አሰፋ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር፣ ዶ/ር ኤርጎጌ ተስፋዬ፣ ዓለም አቀፍና ሀገር አቀፍ አጋር ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ይፋ ተደርጓል።



