Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ተቋማትን አገልግሎት እና ተደራሽነትን ለማሻሻል የሚያግዝ የብድር ስምምነትን ለዝርዝር እይታ መራ

(ዜና ፓርላማ) ጥር 14፣ 2018 ዓ.ም፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በካሄደው 9ኛ መደበኛ ስብሰባው የጤና ተቋማትን አገልግሎት እና ተደራሽነትን ለማሻሻል የሚያግዝ የብድር ስምምነትን ለዝርዝር እይታ መርቷል፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ የተከበሩ ወ/ሮ መሰረት ኃይሌ የብድር ስምምነቱን የኢትዮጵያ መንግሥት የጤና አገልግሎቱን ጥራት እና ተደራሽነት ለማረጋገጥ የተለያዩ ስትራቴጂካዊ ተግባራትን ለማከናወን እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡

የጤና አገልግሎት ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ በመምጣቱ አዳዲስ የጤና ተቋማትን በህክምና መሳሪያዎች ማደራጀት ቀዳሚ ተግባር መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ አክለው ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ፣ የህክምና መሳሪዎች ወጪ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚጠይቅ በመሆኑ፣ የመለዋወጫ እቃዎች እጥረት እና የጥገና ባለሙያዎች አቅም ውስንነት በዘርፉ ላይ ተግዳሮት ሆኖ መቆየቱን የተከበሩ ወ/ሮ መሰረት ኃይሌ አብራርተዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የጤና ተቋማትን ለማደራጀት መንግሥት ከልማት አጋሮች ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝም ነው ያስረዱት፡፡

ለህክምና መሳሪያዎች አቅርቦት ፕሮጀክት ምዕራፍ 2 ማስፈጸሚያ ከደቡብ ኮሪያ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ ጋር የሰላሳ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ቀላል ብድር ስምምነት መፈረሙን ጠቅሰዋል፡፡

ብድሩ የአስራ አምስት ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በአርባ ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ የሚጠናቀቅ እና ከሀገራችን የብድር ስትራቴጂ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጣጣም ቀላል ብድር መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ለዝርዝር እይታ ለፕላን፣ በጀትና እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አዋጅ ቁጥር 5/2018 አድርጉ በሙሉ ድምጽ መርቷል፡፡

(በ-ስሜነው ሲፋረድ)

ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

በፌስቡክ http://www.facebook.com/hoprparliament

በዩቲዩብ

በትዊተር http://twitter.com/fdrehopr

በቴሌግራም

በዌብሳይት www.hopr.gov.et ይከታተሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *