
የፓን-አፍሪካ የቀዶ ህክምና የጤና እንክብካቤ መድረክ በአዲስ አበባ የተከፈተው “ከፖሊሲ ወደ ተግባር፡ የአፍሪካን ባለብዙ ዘርፍ የቀዶ ህክምና የሰው ኃይል ማስፋት” በሚል መሪ ቃል ነው። ዓለም አቀፍ ስብሰባው በአፍሪካ የቀዶ ህክምና እንክብካቤ ስርዓቶችን ለማጠናከር መንገዶችን ለማመቻቸት ከመላው አህጉር የተውጣጡ የጤና ሚኒስትሮችን፣ የህክምና ባለሙያዎችን፣ ተመራማሪዎችን እና ዓለም አቀፍ የጤና አጋሮችን አሰባስቧል።
ፎረሙ አባል ሃገራት ልምድ የሚለዋወጡበት እና ዘርፉን ለማሳደግ ቁርጠኝነታቸውን የሚያረጋግጡበት መሆኑን በመድረኩ የመክፈቻ ንግግራቸው የገለፁት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ፤ ቀዶ ህክምና ለጤና ስርዓት ስርዓት መጠናከር ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ አፍርካዊያን በዘርፉ የሰው ሃብት ልማት፣ ትብብር እና ቀጣይነት ላይ በጋራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
መድረኩ የተጀመረው “የአፍሪካ ባለብዙ ዘርፍ የቀዶ ህክምና የጤና እንክብካቤ የሰው ኃይል፡ እምቅ አቅም፣ እና የወደፊት ተስፋ” በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት ሲሆን ይህም በመላው አፍሪካ ጠንካራ እና ፍትሃዊ የቀዶ ህክምና የሰው ኃይል ለመገንባት ታሪካዊ ተግዳሮቶችን እና የወደፊት እድሎችን ዳስሷል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ልምድ በመድረኩ በዶ/ር ኢሉባቦር ቡኖ፣ የሜዲካል አገልግሎት መሪ ስራ አስፈፃሚ የቀረበ ሲሆን የቀዶ ጥገና አገልግሎቶችን ተደራሽነት ለማስፋት፣ ለጤና ባለሙያዎች ስልጠና ለማሻሻል እና የሆስፒታል መሠረተ ልማትን ለማጠናከር የምታደርገዉ ጥረት ቀርበዋል።



