Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

በክልሉ የሚገኙ ስድስት የንቅናቄ ተቋማት የስራ አፈጻጸም በዱራሜ ከተማ ተገመገመ::

(‎ሆሳዕና፦ጥቅምት 14/2018)፣ ‎በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ ስድስት የንቅናቄ ተቋማት አፈጻጸም የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት አመራሮች በተገኙበት በዱራሜ ከተማ ተገምግሟል።‎የግምገማ መድረኩን የመሩት የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ይሁን አሰፋና የጽህፈት ቤቱ የአደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ይግለጡ አብዛ ናቸው።‎

‎በመድረኩ ጤና፣ገቢ፣ንግድና ገበያ ልማት፣ግብርና፣‎ምግብ ዋስትና እና ስራ ዕድል ፈጠራ በተመለከተ የየተቋማቱ የስራ ሃላፊዎች በጥንካሬና በጉድለት የተለዩ ጉዳዮችን ሪፖርት አድርገዋል።‎‎በተለይም የወባ በሽታ ስርጭት እየተስፋፋ በመምጣቱ በሽታው የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት በተመረጡ የክልሉ አካባቢዎች አመራሩ የተለየ ትኩረት በመስጠት የተጠናከረ የመከላከል ስራ እንዲሰራ ጥሪ ቀርቧል።‎

‎በገቢ አሰባሰቡ የሚታዩ ማነቆዎችን በቅንጅት መፍታት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ጠንካራ ውይይት በማድረግ የመፍትሄ አቅጣጫዎች በመድረኩ ተቀምጠዋል።‎

‎የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች መልካም ቢሆኑም ተጨማሪ መሬቶችን በማረስ ምርታማነትን ማሳደግና የተቀመጠውን ግብ ማሳካት እንደሚገባም አቅጣጫ ተቀምጧል።‎

‎በግብርናው ዘርፍ አዳዲስ ኢንሼቲቮችን በመቅረጽ ወደታች ለማውረድ የተደረጉ ጥረቶችና የተገኙ ስኬቶች በመድረኩ ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ሌሎች ስኬታማ የዘርፉ እንቅስቃሴዎችም ሪፖርት ቀርቧል።‎

‎በንግድና ገበያ ልማት ገበያውን ለማረጋጋት እየተሰሩ ያሉ ስራዎችና ህገወጥነትን ለመከላከል እየተወሰዱ የሚገኙ ህጋዊ እርምጃዎችና አሰራሮች የቀረቡ ሲሆን፤ክልላዊ የስራ ዕድል ፈጠራ ጥንካሬዎች፣ጉድለቶችና የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል።‎

‎በሁሉም የንቅናቄ ተቋማት የተጀመሩ አበረታች ስራዎችን አመራሩና ህዝቡ ይበልጥ ተቀራርበው በመስራት ወደላቀ ደረጃ ማሳደግ እንደሚገባና ማነቆዎቹንም በጋራ መፍታት እንደሚገባም የጋራ አቅጣጫ መቀመጡን ከፓርቲ ጽ/ቤት የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *