
የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ከአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማዕከል ጋር በመተባበር በአፍሪካ የተቀናጀ የመድሃኒት እና የህክምና መሣሪያዎች ግዢ እና አቅርቦት ሜካኒዝም ጅምር ላይ ከፍተኛ ደረጃ ያለው ውይይት አካሂደዋል፡፡ ሜካኒዝሙ አፍሪካ ሲዲሲ በጋራ በሚሰበሰብ ፈንድ የመድኃኒት ምርቶችን እና ክትባቶችን በመግዛት ለአባል ሀገራት ማሰራጨት እና የሃገር ውስጥ ምርትን ለማበረታታት የሚያስችለው ነው።
በዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ የአፍሪካ ዋነኛ የጤና ስርዓት ተግዳሮቶች አንዱ የመድሃኒት እና የህክምና መሣሪያዎች ግዢ እና አቅርቦት መሆኑን ጠቁመዋል። አፍሪካ ሲዲሲ ይህንን አሳሳቢ ችግር ለመፍታት ላደረገው አመራርም አመስግነዋል። ስብሰባው ከተለያዩ ሀገራት የተቀናጀ የመድሃኒት እና የህክምና መሣሪያዎች ግዢ እና አቅርቦት ልምድ ለመቅሰም እና ቀጣናዊ ትብብርን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ፣ እና ሀገራዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ለመለየት ጠቃሚ መድረክ ነው ብለዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ ኢትዮጵያ ለሀገር ውስጥ ፋርማሲዩቲካል ምርቶች ቅድሚያ እንደምትሰጥ ገልጸው፤ በአህጉራዊ ትብብር የአፍሪካ ሀገራት በጋራ ከኤፒፒኤም ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና ዘላቂ የጤና ስርዓቶችን መገንባት እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ውይይቱ በአህጉሪቱ አጠቃላይ የህዝብ ጤና እና የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪ እድገትን ወደ ሚረዳ ወደ አንድ፣ ግልፅ እና ቀልጣፋ የግዥ ሂደት ለማምጣት ክልላዊ ጥረቶችን በማጣጣም ረገድ ትልቅ ምዕራፍን አሳይቷል። ኢትዮጵያ የተቀናጀ የመድሃኒት እና የህክምና መሣሪያዎች ግዢ እና አቅርቦት ትግበራ ለመጀመር የመግባቢያ ሰነድ ከፈረሙ 10 ሃገራት አንዷ ናት፡፡



