
ለሁሉ አቀፍ የጤና አገልግሎት አዳዲስ የኢኖቬሽን ስራዎች ተግባራዊ ይደረጋሉ – ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ
(ሆሳዕና፣ ሰኔ 20/2017)፦ በኢትዮጵያ ለሁሉ አቀፍ የጤና አገልግሎት አዳዲስ የኢኖቬሽን ስራዎች ተግባራዊ እንደሚደረጉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ተናገሩ።
“ኢኖቬሽን ለሁለንተናዊ የጤና ሽፋን” በሚል መሪ ሃሳብ ላለፉት ሶስት ቀናት በአዲስ አበባ ሲካሔድ የነበረው አለም አቀፍ የጤና ኢኖቬሽንና ጥራት ጉባኤ ተጠናቋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ፍትሃዊነትን መሰረት ያደረገ የጤና ስርዓት እየተገበረች ትገኛለች።
በዚህም በጤና አገልግሎት ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ጠቅሰው በቀጣይም አዳዲስ የኢኖቬሽን ስራዎችን በመተግበር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በጤናው ዘርፍ በኢኖቬሽን የተደገፉ አሰራሮችን በመተግበር ተጠያቂነትን የማስፈንና ሰው ተኮር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል።
አለም አቀፉ ማህበረሰብ በጤናው ዘርፍ ተግባራዊ የሚደረጉ አዳዲስ የኢኖቬሽን ስራዎችን በመደገፍ ረገድ ትብብሩን እንዲያጠናክር ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ጉባኤው በጤና ኢኖቬሽን ዘርፍ የጋራ ራዕይን ለማሳካት ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።
ኢኖቬሽን የቅንጦት ጉዳይ አለመሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ የጤና ጥራት፣ ተደራሽነትና የህሙማን ደህንነትን የበለጠ ለማጠናከር ያለውን ቁልፍ ሚና ገልጸዋል።
በመሆኑም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የጤናውን ዘርፍ የሚያሳልጡ የኢኖቬሽን ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ ኢትዮጵያ የስታርታፕን በሁሉም ዘርፍ ለማበረታታት ረቂቅ ፖሊሲ ማዘጋጀቷን አስታውሰው፤ በጤናው ዘርፍ የሚመጡ ስታርታፖችን ወደ ተግባር ለመቀየር አበረታች እንደሆነ ጠቁመዋል።
የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል(አፍሪካ ሲዲሲ) ሳይንስና ኢኖቬሽን ዳይሬክተር ሞሶኮ ፋላ የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቱ ያለውን አቅም በመጠቀም የማምረት አቅምን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያላት የምርምር አቅምና በመሰረተ ልማት እያከናወነች ያለውን ኢንቨስትመንት አድንቀው፤ ማዕከሉ በትብብር መስራቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።


