
(ሆሳዕና:- ሰኔ 20/2017) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በክልሉ በሚገኙ የዱቄትና ዱቄት ውጤት አምራቾች ጋር በንጥረ ነገር የበለፀገ ምርት ማምረት የሚያስችል የምክክር መድረክ በቡታጅራ ከተማ እያካሄደ ነው።
የማዕከላዊ ኢትዮዽያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ የምግብ ደህንነትን በማረጋገጥ በአካልና በአእምሮ ላይ የሚያጋጥመንን የጤና እክል መከላከል ይገባል ብለዋል።
በክልሉ የሚገኙ በዱቄት ፋብሪካ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች ምርታማነትን በማሳደግ ለሀገሪቱ እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እየተወጡ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ሳይበለፅግ ወደ ገበያ የሚወጣ ዱቄት የህፃናትን እና የእናቶችን ጤና መጉዳት ነው ያሉት አቶ አንተነህ ምግብን ማበልፀግ ህግ ከማስከበር ባለፈ የሞራል ጉዳ መሆን አለበት ብለዋል።
የበለፀገ ዱቄት መመገብ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚሞቱትን እናቶችና ህፃናት ህይወት መታደግ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም አምራች የበለፀገ ዱቄት ማምረት ይገባዋል ብለዋል።
የዱቄት ንጥረ ነገር እጥረት ያልታወቀበት ረሀብ ነው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በዜጎች ላይ ከጤና እክል ባለፈ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ በመፍጠር ሀገርን ይጎዳል ብለዋል።
የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ አባስ መሐመድ (ዶ/ር) እንደገለፁት በክልሉ የምግብ ዱቄትን በንጥረ ነገር ለማበልፀግ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የምግብ ደህንነት ጉዳይ ከማምረቻው ጀምሮ በልዩ ትኩረት መመራት እንደሚገባው ያነሱት ሀላፊው በተመጣጠነ የአመጋገብ ሥርዓት እጥረት ምክንያት የሚመጣን ችግር ለመከላከል ተቋማት ተቀናጅተው መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
መድረኩ በክልሉ ለስንዴ ዱቄት አምራች ኢንዱስትሪዎች ግንዛቤ በመፍጠር የስንዴ ዱቄት ማሟላት ያለበትን ዝቅተኛ መመዘኛ መስፈርት በማሟላት ወደ ትግበራ ለመግባት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣ ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ እንደተናገሩት ከስነ-ምግብ እጥረት ውስጥ አንዱ የሆነው የንጥረ ነገር መጓደል ነው ብለዋል።
የንጥረ ነገር መጓደል ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር በአካልና የአእምሮ እድገት ላይ የጤና እክል ያመጣል ብለዋል።
አምራች ህብረተሰብ በማቀንጨር በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ችግር ይፈጥራል ያሉት ዳይሬክተሯ መንግስት የስነ ምግብ እጥረት ለመቅረፍ ምግብን በቫይታሚንና ሌሎች ማዕድናት ለማበልፀግ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በመድረኩ የክልሉ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎን ጨምሮ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም የእንዱስትሪ ባለቤቶች እና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፊ ይገኛሉ።
የክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን



