Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኤም ፖክስ (Mpox) በሽታ ቅድመ መከላከል ስራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን የክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ::

ኤም ፖክስ ወይም በተለምዶ የዝንጀሮ ፈንጣጣ በመባል የሚታወቀው በከፍተኛ ፍጥነት ከሚሰራጩ በሽታዎች አንዱ መሆኑንና የአለም አቀፍ የጤና ስጋት ሆኖ የተመዘገበ በሽታ መሆኑን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን ከደቡብ ሬዲዮ ቴሌቪዥን ድርጅት ጋር ባደረጉ ቆይታ ተናግረዋል።

የኤም ፖክስ ቫይረስ የተገኘባቸው ግለሰቦች እንደ ሽፍታ፣ ሳል፣ ትኩሳት፣ የራስ ምታት፣ የንፍፊት ማበጥ፣ የቆዳ ቁስለትና ድካም፣ የጡንቻና የጀርባ ህመም ምልክቶች የሚታይባቸዉ መሆኑን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር የተናገሩ ሲሆን፤ በሽታው በተለይም ታማሚዎች አካል ላይ ቁስል ካለ በቀላሉ የሚተላለፍ ሲሆን በንክኪ እና የቅርብ ትንፋሽ ግንኙነት ዋነኛ መተላለፊያ መንገዶች ናቸዉ ብለዋል።

በክልል ደረጃ በሽታው ያለበትን ደረጃ የሚከታተል ግብረ ሃይል ተቋቁሞ በየቀኑ በክልሉ መዋቅር የመገምገም ስራ እየተሰራ መሆኑን አቶ ማሙሽ ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ከኤም ፖክስ በሽታ ራሱን ለመጠበቅ የኤም ፖክስ ምልክቶች ካሉባቸው ታማሚዎች ንክኪ በመቀነስ፣ ታማሚዎቹ የተጠቀሙባቸውን ቁሳቁሶች፣ አልባሳትና መኝታ በአግባቡ ሳያጸዱ ባለመጠቀም፣ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛዎችን በመጠቀም፣ የግል እና የእጅ ንፅህና በመጠበቅ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ እያሳሰብን የኤም ፖክስ ምልክቶች የሚያሳይ ማንኛዉም ሰው በሚገኝበት ወቅት ወደ ህክምና ቦታ መሄድ ይገባዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ግንቦት 17/2017 ዓ.ም በላብራቶሪ ምርመራ ኤም ፖክስ እንደተገኘ የተረጋገጠ ሲሆን፤ በኦሮሚያ ክልል ሞያሌ ከተማ አስተዳደር የ21 ቀን ህጻን በበሽታው መያዙ መረጋገጡ እና በተደረጉት ቀጣይ ምርመራዎች የህጻኑ እናት እንዲሁም ወደ ጎረቤት ሃገር የጉዞ ታሪክ ያለው የህጻኑ አባት ኤም ፖክስ እንደተገኘባቸው ለማረጋገጥ መቻሉን የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ ያመላክታል፡፡

በዚህም መሰረት ይህ መረጃ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ 19 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን መረጃው አመላክቷል።

ዘጋቢ: ፋሲል ኃይሉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *