
በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የድንገተኛ ህክምና ቡድን (Emergency Medical Team – EMT) የተሟላ የመስክ ልምምድ (Full Scale Simulation Exercise) ተካሄደ::
የብሔራዊ አደጋ ምላሽ አቅምን ለማጠናከር ትልቅ እርምጃ የሆነው የልምምድ መርሃግብሩ የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) ከ UK MED እና UK Emergency Medical Team (UK EMT) ጋር በመተባበር በሀገሪቱ የመጀመሪያውን የተሟላ የድንገተኛ ህክምና የመስክ ልምምድ “የማይበገር የህብረተሰብ ጤና አደጋ አስተዳደር ወደ የተሟላ የልህቀት ማዕከል” በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል።
“ይህ ልምምድ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የአደጋ ጊዜ ምላሽ ሥርዓት ለመገንባት በምናደርገው ጉዞ ወሳኝ ምዕራፍ ነው” ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ገልፀዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግስት የአለም የጤና ድርጅት ባወጣው መለኪያ መሰረት ዓይነተ አንድ የአደጋ ጊዜ የህክምና ቡድን (Type 1 Fixed EMT) አለም አቀፍ ደረጃን ለማግኘት የሚያስችሉ ሙሉ ግብዓቶች ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፤ በመርሀ ግብሩ የግብአቶች ድጋፍ ብቻ ሳይሆን የዕውቀት ሽግግርም ተደርጎበታል። “ይህ የልምምድ መርሀ ግብር ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ የጤና ስርዓትን በመገንባት ላይ ያለንን አጋርነት አንዱ ማሳያ ሆኖ ያገለግላል” ያሉት በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ዳረን ዌልች ናቸው።
የተደረገው ድጋፍ እና የልምምድ መርሃ-ግብር የሃገራችንን የድንገተኛ አደጋ ምላሽ አሰጣጥ አንድ እርምጃ ወደፊት ያራመደ መሆኑን የገለጹት የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሳይ ኀይሉ ናቸው።
በዝግጅቱ ላይ የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር፣ የክልል ጤና ቢሮዎች፣ አለም አቀፍ ኤጀንሲዎች እና ከአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠር ድርጅትም ተገኝተዋል።
በመድረኩ የፓናል ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ ለወደፊቱ በትብብር ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድም ተፈርሟል።