Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

የወባ በሽታን ለመከላከል በምርምር የተገኙ አዳዲስ ውጤቶችን በግብዓትነት መጠቀም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ሆሳዕና ፤ ሚያዝያ 16/2017፡ – የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በምርምር የተገኙ አዳዲስ ውጤቶችን በግብዓትነት መጠቀም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በወባ በሽታ ላይ ያተኮረ አስራ አምስተኛው ሲምፖዚየም እየተካሄደ ነው።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉ በሲምፖዚየሙ መክፈቻ ላይ እንዳሉት፤ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በጥናት የተለዩ ውጤቶችን መተግበር ያስፈልጋል።

ኢንስቲትዩቱ በጤና ላይ ጥናትና ምርምሮችን ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው፤ የወባ በሽታን ለመከላከልም ጥናትና ምርምር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በጥናትና ምርምር የተገኙ አዳዲስ ግኝቶችና ውጤቶች ከተመራማሪዎች ጋር በመወያየት የፖሊሲ ግብአት መሆን እንዲችሉ መስራት እንደሚገባ ተናግረው ባለድርሻ አካላት የምርምር ውጤቶችን እንዲጠቀሙ የማመቻቸት ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በጤና ሚኒስቴር የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ህይወት ሰለሞን በበኩላቸው፤ በየዓመቱ በሚካሄደው ሲምፖዚየም ላይ በወባ በሽታ ዙሪያ በሚደረጉ የጥናትና ምርምር ስራዎች ላይ ውይይት እንደሚደረግ ገልጸዋል።

በተለይም በሽታውን ከመከላከል አኳያ የሚገጥሙ ችግሮች፣ የመድሀኒት አወሳሰድና የስርጭት ሁኔታዎችን አስመልክቶ በጥናት የተገኙ ውጤቶች ላይ ይመከራል ብለዋል።

በዚህ ሲምፖዚየም የተለያዩ በበሽታው ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው የዘርፉ ምሁራን አስተያየት እንደሚሰጥበት ጠቅሰው፤ በጤና ዙሪያ የሚሰሩ ባለድርሻ አካላት የጥናትና ምርምር ግኝቶችን ለበሽታ መከላከል ስራው ሊጠቀሙበት እንደሚገባ አመልክተዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ጀማል አባ ፊጣ(ዶ/ር)፤ ዩኒቨርሲቲው በጥናትና ምርምር የጤናውን ዘርፍ እያገዘ እንደሆነ ገልጸዋል።

በተለይም በወባ በሽታ ላይ ያተኮረ የምርምር ማዕከል በመገንባት በርካታ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል።

የትምህርት ተቋሙ ከጥናትና ምርምር ባሻገር የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ በሽታን በመከላከል እና በመቆጣጠር በኩልም የበኩሉን እየተወጣ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

በሲምፖዚየሙ የተለያዩ የዘርፉ ምህራን እና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ሲሆን ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ ታውቋል።

ምንጭ #ኢዜአ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *