Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

በጤናው ዘርፍ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሳይንሳዊ ምርምር በማስደገፍ የህዝብ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ተመላከተ

(ሆሳዕና፣ጥር 24/2017 )የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ከአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በባህላዊ መድሀኒት ጥናት ላይ በትብብር መስራት የሚያስችል የመግባቢያ ውል ስምምነት ተፈራረሙ

የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንደገለጹት ተመራማሪዎች እና የዘርፉ ባለሙያዎች የህዝቡን የጤና ችግሮች መፍታት የሚችሉበትን እድል መፍጠር ይገባል ብለዋል።

በክልሉ ካሉ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ቅንጅት በመፍጠር በጤና ልማት ስራ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ስራ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም ዋና ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።

ሀገር በፍጥነት እንድታድግ ቅንጅታዊ ስራ አስፈላጊ ነው ያሉት

ፕሮፌሰር አፈወርቅ ያሉንን ጸጋዎች በመለየት እና ምርምር በማካሔድ በዘርፉ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ መስራት ተገቢ ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት የተጣለበትን ሀገራዊ ሀላፊነት በብቃት መወጣት የሚችል የኢትዮጵያ ህዝብ ተቋም ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ የጤና ልማት ስራዎችን በምርምር ላይ ተመስርቶ እያከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።

ምርምርን ከልማት እንዲሁም የጤና የፈጠራ ስራዎችን ከትግበራ ጋር በማቀናጀት እየተሰራ ስለመሆኑ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ የመድሀኒት፣የክትባት፣የህክምና እና የምርመራ መሳሪያዎች ልማትን እና ኢንዲስትሪን እንዲደግፉ በማድረግ ረገድ ተቋሙ የተጣለበት ኃላፊነት የላቀ መሆኑን አስታውቀዋል።

ኢንስቲትዩቱ በክልሉ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች እና ከጤና ቢሮ ጋር በበርካታ ጉዳዮች በትብብር ሲሰራ እንደነበር ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ በዘርፉ የሚካሔደውን የጤና ልማት ስራ ውጤታማ ለማድረግ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ ስለመሆኑም አመላክተዋል።

የክልሉን የጤና ልማት የትኩረት መስኮች መለየት እና የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች በሳይንሳዊ ምርም መፍታት የሚቻልበትን ስርዓት ማጠናከር እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት በጤና ምርምር፣በፈጠራ፣በቴክኖሎጂ ሽግግር፣በሰው ሀብት ልማት ፣በኢንዳስትሪ ልማት እና በሌሎችም ዘርፎት ትኩረት በማድረግ እየሰራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ እንደገለጹት በክልሉ የጤና ልማት ስራውን ውጤታማ በማድረግ ረገድ የምርምር ተቋማት ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የምርምር ኢንስቲትዩቱ ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በትብብር ለመስራት ያለውን ዝግጁነት አቶ ሳሙኤል አድንቀዋል።

በክልሉ በህክምና አገልግሎት ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ያሉ ሶስት ሞዴል ሆስፒታሎች እንዳሉም ኃላፊው አብራርተዋል።

በክልሉ ከ 7 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ህዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የመጀመሪያ ደረጃ 24 ጀነራል ሆስፒታል 4 እንዲሁም ኮምፕርሄንሲፍ ሆስፒታል 2 ሆስፒታሎች እንዳሉም ኃላፊው አመላክተዋል።

ክልሉ ሰላማዊ መሆኑን ተከትሎ የጤናውን ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ ተመራማሪዎች በየትኛውም አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው መስራት እንደሚችሉም አቶ ሳሙኤል አብራርተዋል።

የዘርፉ ተመራማሪዎች በክልሉ በጤናው ዘርፍ የሚያጋጥሙ ችግሮች እና የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በትኩረት መስራት የሚችሉበትን ስርዓት ተዘርግቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በበኩላቸው በጤናው ዘርፍ የሚካሔደውን ሁሉን አቀፍ ጥረት ውጤታማ ለማድረግ የእውቀት ሽግግር እና ቅንጅታዊ ስራ ወሳኝ ነው ብለዋል።

በዘርፉ የሚካሔዱ ሳይንሳዊ ጥናቶች ተግባራዊ ሆነው በጤና ልማት ላይ አዎንታዊ ሚና እንዲኖራቸው ከምርምር ተቋማት ጋር በትብብር መስራት አስፈላጊ ስለመሆኑም ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

በክልሉ መሰረታዊ የሆኑ የጤና ችግሮችን በመለየት የጥናትና ምርምር ስራ ተግባራዊ እየተደረገ ነው ያሉት አቶ ማሙሽ ባህላዊ መድሀኒቶች በዘመናዊ ህክምና ላይ የሚኖራቸውን አስተዋጽኦ ማመላከት ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።

በመርሐ ግብሩ የክልል ከፍተኛ የስራ ኅላፊዎች፣ተመራማሪዎች፣ከወራቤ፣ከወልቂጤ እና ከዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *