
የጤና ኤክስቴንሽኖች የተሃድሶ ስልጠና መስጠት መጀመሩን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ አስታውቋል።
ከክልሉ ስልጤ፣ ጉራጌ፣ ምስራቅ ጉራጌ፣ እና ሀላባ ዞኖች ከተመረጡ ወረዳዎች ለተውጣጡ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የሚሰጠው ስልጠና በዛሬው ዕለት በወራቤ ዩኒቨርሲቲ ተጀምሯል።
የቢሮው ሃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በክልሉ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙን ለማጠናከር በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑ በመግለጽ በበጀት ዓመቱ ከታቀዱ ተግባራቶች አንዱ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን ዓቅም ማጎልበት መሆኑን አስገንዝበዋል።
የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የጤናውን ሴክተር ተግባር ለማሳለጥ የጀርባ አጥንት ሆኖ እያገለገለ መሆኑን ያመላከቱት ኃላፊው ወቅቱን በሚመጥን ዘመናዊ የአሰራር ስርዓት (digitalization) ላይ ያተኮረ ስልጠና ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች መስጠት ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በማህበረሰቡ ላይ የሚያደርሰውን ቀውስ በእጅጉ በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ የታመነበት መሆኑን አስረድተዋል።
ይህ አሰራር በጤናው ዘርፍ የሚጠበቀውን ውጤት ከማረጋገጥ ባሻገር የማህበረሰቡን የጤና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የአገልግሎት ጥራትን በማስጠበቅ የህክምና ተጠቃሚዎችን እንግልት የሚቀንስ መሆኑንም አክለዋል።
አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ የቢሮ ምክትልና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊ በበኩላቸው መከላከልን መሠረት ባደረገው የጤና ፖሊሲ ላይ በመመስረት ተግባራት መፈጸም እንደሚገባ በመጠቆም ይህንኑ ግብ ለማሳካት የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን ዓቅም ለማጎልበት እና ፕሮግራሙን ለማጠናከር የክልሉ ጤና ቢሮ ከምንጊዜውም በተሻለ በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።
የህብረተሰቡን የጤና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ፋይዳው የጎላ ነው ያሉት አቶ አሸናፊ በተመደቡበት ጤና ኬላ ስራቸውን በኃላፊነት የሚወጡትን ባለሙያዎች የማበረታታት ስራን አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ማለታቸውን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል።
