
ጥራቱን የጠበቀ የምጥና የወሊድ አገልግሎት በመስጠት በእናቶችና ህጻናት ላይ የሚደርሰውን ሞት ለማስቀረት በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተመላከተ
(ጥር19/2017 )በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጤናማ እናትነት ወር ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሆሳዕና ከተማ እየተካሔደ ነው
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ እንደገለጹት የጤናማ እናትነት ወር መከበር አብይ ዓላማ የእናቶችንና የህፃናትን ጤና በማሻሻል ጤናማ ህብረተሰብን ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል።
እናቶች መከላከል በሚቻሉ ምክንያቶች የሚደርስባቸውን ህመምና ሞት ለመታደግ በዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት መስራት ይገባል ብለዋል።
ጥራቱን የጠበቀ የምጥ እና የወሊድ እንክብካቤ ለጤናማ እናትነት የሚኖረው አበርክቶ ከፍተኛ ስለመሆኑም ነው ኃላፊው የተናገሩት።
ለእናቶችና ህጻናት ሞት በምክንያትነት ከሚጠቀሱት ችግሮች መካከል እናቶች ፈጥነው ወደ ጤና ተቋማት በመሔድ አገልግሎት ለማግኘት መዘግየት የችግሩን አሳሳቢነት ከፍ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል።
እናቶች ወደ ጤና ተቋም ለመሔድ በትራንስፖርት እና ተያያዥ ችግሮች ምክንያት በሚያጋጥም መዘግየት የሚከሰት ሞት እንዲሁም በጤና ተቋማት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚስተዋል ውስንነት ሌላኛው ተግዳሮት ስለመሆኑም አቶ ሳሙኤል አብራርተዋል።
በጤና ተቋማት ከእናቶች እና ህጻናት ሞት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥመውን ችግር ለመታደግ የአንቡላንስ አቅርቦትን ማሻሻል እና ሌሎች የህክምና ግብአት ማሟላት ተገቢ መሆኑን ኃላፊው ጠቁመዋል።
በክልሉ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተሞክሮነት የበቃው የነፍሰ ጡር እናቶች ማቆያ በጉራጌ ዞን አጣጥ ሆስፒታል ተግባራዊ መደረጉን የተናገሩት አቶ ሳሙኤል ይህም በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች እንዲስፋፋ መደረጉን በአብነት ጠቅሰዋል።
በክልሉ የእናቶችን እና ህጻናትን ጤና ለመጠበቅ ከሚረዱ አብይ ጉዳዮች መካከል የማህጸን በር ጫፍ ካንሰር ምርመራ እና ህክምና ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን አስመልክቶ ህብረተሰቡን ማስገንዘብ እንደሚገባ አቶ ሳሙኤል አመላክተዋል።
በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ የንግስት ኢሌኒ መሃመድ መታሰቢያ ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ይድነቃቸው ደዳቸው እንደገለጹት በሆስፒታሉ ለእናቶችና ለህጻናት ምቹ የህክምና አገልግሎት መስጠት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በሆስፒታሉ ከ800 እስከ 1ሺ የሚደርሱ እናቶች የወሊድ አገልግሎት እያገኙ ነው ያሉት ዶ/ር ይድነቃቸው በዘርፉ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ የማስፋፊያ ስራ ተግባራዊ ለማድረግ የቅድመ ዝግጅት ስራ መጠናቀቁን አብራርተዋል።
ከዋቸሞ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር የእናቶች እና ህጻናት ማዕከል ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን አብራርተዋል።
በሆስፒታሉ የእናቶችና ህፃናት የህክምና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽ ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡የማኢክመኮ

