
ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ -የጤና ሚኒስትር ሚኒስትር ዲኤታ
የጤና ሚኒስትር ሚንኒስትር ዴዔታ ክብርት ወይዘሮ ፍሬሕይወት አበበ በማረቆ ልዩ ወረዳ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት የሱፐርቪዥኑ ዋነኛው ዓለማ በልዩ ወረዳው ከዚህ በፊት የወባ በሽታ ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተደረጉ ያሉ ተግባራትና በበሽታው ተይዘው ህክምና ለሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች የሚሰጠውን ህክምና ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆን የሚያስችል ድጋፍና ክትትል መሆኑን ገልጸው የወባ በሽታ በተከሰተባቸው ቦታዎች በመከላከልና በመቆጣጠር ስራው ላይ ክፍተቶችን በመለየት መፍትሄ እንዲሰጥ የሚያደርግ እንደሆነም ተናግረዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በበኩላቸው በክልሉ በጤናው ዘርፍ የሚሰሩ በርካታ ስራዎች እንዳሉ ጠቅሰው አሰራሮቹን ማዘመንና ማሻሻል የሁሉንም ማህበረሰብ የህክምና አገልግሎት ፍላጎት ተደራሽ በማድረግ በክልሉ የወባ ወረርሽኝን ለመከላከል ለመቆጣጠር ከጤና ሚኒስትርና ከሁሉም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንዲሰሩም ገልጸዋል።
በጤና ሚኒስቴር የአርመወርሃንሰን የምርምር ኢኒስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተርና የተቀናጀ የወባ በሽታ ክትትልና ድጋፍ ልዑክ ቡድን አስተባባሪ ረዳት ፕሮፌሰር መሳይ ወልደ ማሪያም በድጋፍና ክትትል ወቅት ተገኝተው እንዳሉት የወባ በሽታን ለመከላከል ለመቆጣጠር እየተሰራ ያለው ስራ አበረታች ቢሆንም ለዚህ ጉዳይ ይረዳ ዘንድ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ከማሻሻል አኳያ ግንዛቤ የመስጠቱ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በመተባበር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል።
በአገር ዓቀፍ ደረጃ በሁሉም ክልሎች የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በክልሎች በኩሉ የተጀመሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ በጤና ሚኒስቴር ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራም ረዳት ፕሮፌሰሩ አስገዝበዋል።
የማረቆ ልዩ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ጀማል አማሮ በዚህ ወቅት እንዳሉት በልዩ ወረዳ የወባ በሽታን መከላከልና መቆጣጠር እንዲቻል ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ገልጸው ለዚህም የአገልግሎት መሳለጥ የአመራሮች፣ የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም ግብረ ኃይሎች እያደረጉ ያሉት አስተዋጽኦ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ወባ እያደረሰ ካለው ጉዳት አንጻር ስራው ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የመዳሃኒት አቅርቦት እጥረት እንዳይኖር ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሆነ ገለጸዋል።
በጤና ሚኒስቴር የተቀናጀ የወባ በሽታ ክትትልና ድጋፍ ልዑክ ቡድን መላኩ ወረርሽኙ ማህበረሰቡ ላይ የከፋ ችግር ሳያደርስ በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ያግዛል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው የተጀመሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የህክምና ግብአት አቅርቦትና አጠቃቀምን፣ የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ስራዎች ጥራት ባለው መልኩ ውጤታማ ሆነው እንዲቀጥሉ በምልከታው የሚገኘው ግብረ መልስ አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የጤና ሚኒስትር ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ፍሬህይወት አበበ የተመራ ሉዑካን ቡድን ትኩረቱን በወባ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር እንዲሁም በመጀመርያ ጤና ክብካቤ ላይ ያደረገ የተቀናጀ ድጋፍዊ ክትትሉን የወባ በሽታ ስርጭት ስጋት አለባቸው ተብለው በተለዩ በሾኔ ከተማ የመጀመርያ ደረጃ ሆስፒታል ምልከታና ውይይት አድርጓል።
የጤና ሚኒስትር የወባ መከላከልና መቆጣጠር ግብረ-ኃይል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ማረቆ ልዩ ወረዳ እና ሾኔ ከተማ አሰተዳደር በመገኘት በወባ በሽታ ወረርሽኝ መከላከልና መቆጣጠር ላይ ያተኮረ ውይይት እና ምልከታ አድርጓል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የጤና ሚኒስትር ሉዑካን ቡድን በስልጤ ዞን ወረቤ ከተማ በመገኘት የክልሉ ጤና ቢሮና የወራቤ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ በመገኘት ጎብኝቷል።
የማ/ኢት/ክ/ጤና ቢሮ


