
በክልሉ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት የተከሰቱ ወረርሽኞችን መከላከልና መቆጣጠር መቻሉ ተገለፀ።
ሆሳዕና ህዳር 25/2017
በማዕከላዊ ኢትዮጵያዊ ክልል ጤና ቢሮ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ዳይሬክቶሬት የ5 ወር አፈፃፀም ግምገማ መድረክ በወራቤ ከተማ ተካሂዷል።
የቢሮው የህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን እንደገለፁት በድንገተኛ አደጋዎች በወረርሽኝ መልክ የሚከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጠንካራ ስራ መሰራቱን ገልፀዋል።
በክልሉ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት የተከሰቱ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የክልሉ መንግስትና በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ጉልህ ሚና እንደነበረውም ተናግረዋል።
በተቋማት ለድንገተኛ አደጋ ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል አቅም መገንባት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አቶ ማሙሽ ተናግረዋል።
ማህበረሰቡን ከየትኛውም የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የጤና ስጋት ለመጠበቅ ከመደበኛ የጤና አደረጃጀት ጎን ለጎን ድንገተኛ አደጋዎችን ቀድሞ የመለየትና የመከላከል ስራ ተጠናክሮ መሰራት ይገባዋል ብለዋል።
በመድረኩ የሪፖርት ሰነድ ያቀረቡት የኢንስቲትዩቱ የጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወልደሰንበት ሸዋለም በክልሉ ከ1300 በላይ የመንግስትና የግል የጤና ተቋማት መኖራቸውንና የህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ቁጥጥር ስራው ተጠናክሮ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ የወባ፣ የኮሌራ ፣ የኩፍኝ ፣የምግብ እጥረት ፣ የጎርፍና የእሳት አደጋ መከሰቱን የተናገሩት አቶ ወልደሰንበት አደጋዎችን ቀድሞ ቅኝት በማድረግ ለህብረተሰቡ ቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ምላሽ የመስጠት ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
አሁንም በየአካባቢው የወባና ሌሎችም በሽታዎች ስርጭት በመኖራቸው የተጀመሩ ማህበረሰብ ተኮር ስራዎች ተጠናክሮ የቤት ለቤት ክትትልና ልየታ በትኩረት መሰራት አለበት ብለዋል።
የኢንስቲትዩቱ ላቦራቶሪ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ወንድሙ በክልሉ ዘመናዊ የላብራቶሪ ስርዓት ለመዘርጋት የአገልግሎት ጥራት ማሻሻያ ዘዴዎች ዙሪያ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የተቋማትን የቁሳቁስ እጥረት በመቅረፍ ለዜጎች የላብራቶሪ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።



