የአለም የስኳር ቀን በሃገራችን ለ34ኛ ጊዜ ህዳር 5 ይከበራል፡፡ የዘንድሮውን በአል ጤና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር እና አጋሮቹ “የስኳር ህመምና ምሉዕ ደህንነት፡- ለስኳር ህመም ህክምና እና ክብካቤ ተገቢውን ተደራሽነት ካገኙ ሁሉም የስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች በተሟላ ጤንነት የመኖር እድል አላቸው!” በሚል መሪ ቃል የሚከበር ይሆናል፡፡
በዓሉ ትኩረት የሚያደርገው የስኳር ህመም ህክምና እና ክብካቤ ተደራሽነት ዙሪያ፤ ከስኳር ህመም ጋር የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የስኳር ህመም ከተከሰተ በኋላ አስፈላጊውን ህክምና፣ ክብካቤ፣ መድሃኒት፣ እና የስኳር መመርመሪያ አቅርቦት ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግ መሆኑን የገለጹት በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከል እና መቆጣጠር መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ህይወት ሰለሞን፤ የስኳር ህመም በሃገራችን በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ የሚገኝ ተላላፊ ያልሆነ በሽታ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በሃገራችን ከ1.9 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከስኳር ህመም ጋር እንደሚኖሩ ይገመታል፡፡ ችግሩን አስከፊ የሚያደርገው 50 በመቶ የሚሆኑት ህሙማን ምንም አይነት የስኳር ምርመራ ያላደረጉ በመሆናቸው ህክምና እያገኙ አይደለም፡፡ በሃገራችን የአይነት አንድ የስኳር ህመም በህጻናት እና ወጣቶች ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱን ዶ/ር ህይወት ተናግረዋል፡፡
ለስኳር ህመም አጋላጭ ሁኔታዎችን ያብራሩት ደግሞ የኢትዮጵያ የስኳር ህመም ማህበር ፕሬዘዳንት ዶ/ር ጌታሁን ታረቀኝ ሲሆኑ፤ በተለይም ከቅጥ ያለፈ ውፍረት በከፍተኛ ደረጃ ለስኳር ህመም እንደሚጋልጥ አስረድተዋል፡፡ እስከ 80 በመቶ የሚሆነውን የአይነት ሁለት የስኳር ህመም ጤናማ አመጋገብን በመከተል፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ፣ ሲጋራ ማጨስን በማቆም ጤናማ አኗኗርን በመከተል መከላከል እንደሚቻልም ገልጸዋል፡፡
ጤና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማህበር እና አጋሮቹ ጋር በመተበበር የስኳር ህመም ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ በስኳር አጋላጭ መንስኤዎች ዙሪያ በፖሊሲ የተደገፈ የመከላከል ስራ መስራት እና የስኳር ህመም ቅድመ ምርመራ፣ ምርመራ፣ ህክምና እና ክብካቤ አገልግሎት ማስፋፋት እና የማጠናከር ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ህዳር 5 የሚከበረውን የአለም የስኳር ህመም ቀንን አስመልክቶ በጤና ሚኒስቴር ግቢ ውስጥ ለሰራተኞች ነጻ የስኳር ህመም ምርመራ ተደርጓል፡፡