በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የጤና ምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ የጥናትና ምርምር ጉባኤ በወራቤ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ዉስጥ እየተካሄደ ነዉ።
ዶ/ር ኢንጂነር ቶፊቅ ጀማል የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮግራሙን በከፈቱበት ወቅት እንደገለፁት መንግስት በ4ኛዉ ትዉልድ ከመሠረታቸው 14 ዩንቨርሲቲዎች መካከል የወራቤ ዩኒቨርስቲ አንዱ መሆኑን ጠቅሰው መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደቱን በ2010 ዓ/ም የጀመረ ሲሆን ዩንቨርሲቲዉ ሲጀምር በ4 ኮሌጆች ስር 14 የት/ት ክፍሎች ነበሩት። አሁን በተደረገው ከፍተኛ ርብርብ 6 ኮሌጆች፣ 2 ት/ት ቤቶች እንዲሁም አንድ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሲኖሩት በ9 አካዳሚ መዋቅሮች ከ6ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛ እና በቅድመ መደበኛ ትምህርት ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል።
ፕሬዝዳንቱ አክለዉም የጤና አገልግሎትን ጥራት ለመጨመር ለጤና ባለሙያዎች ወቅቱን የጠበቀ ተከታታይ የሙያ ስልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልፀው ከጤና ቢሮ ጋር በማንኛዉም መልኩ ለመደጋገፍና በጋራ ተቀናጅቶ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸዉን አስረድተዋል።
አቶ ሽመልስ ዋንጎሮ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ በመልዕክታቸው ጥናትና ምርምር መካሄዱ የሰው ልጆች በህይወት የመኖር ምጣኔ 68.7 ከፍ ያደረገ ሲሆን ይህ ዉጤት የተገኘው በጥናትና ምርምር በመታገዝ ነው ብለዋል።
ሀላፊው አክለውም በስነ-ምግብ እና በተለያዩ የሕብረተሰብ ጤና ችግሮች ላይ ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናት እና ምርምሮችን ማድረግ፣ በጥናትና ምርምር ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስራዎችን መስራት፣ የጥናትና ምርምር ዉጤቶችን ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ማሰራጨት፣ ከፍተኛ ልምድ ባላቸዉ ተመራማሪዎች ጥራት ያላቸውን ጥናትና ምርምሮችን ማካሄድም ቀጣይ የትኩረት መስኮች መሆናቸውን አውስተዋል፡፡
አቶ ማሙሽ ሁሴን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስትቱዩት ዋና ዳይሬክተር በዚሁ እለት እንደተናገሩት የክልሉ የህብረተሰብ ጤና እንስቲትዩት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የክልሉን ማህበረሰብ ከበሽታና ከተለያዩ ድንገተኛ የማህበረሰብ የጤና ጠንቆች በጥናትና ምርምር፣ በከፍተኛ የላብራቶሪ ምርመራ አገልግሎቶች፣ በድንገተኛ አደጋዎች ቅኝትና ምላሽ እንዲሁም የክልሉን የጤና መረጃ አያያዝ ለዉሳኔ መጠቀም ዋና ተልዕኮ አድርጎ በመያዝ፣በሽታን በመከላከል እና በመቆጣጠር እያገለገለ ይገኛል ብለዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም የተለያዩ ምርምሮች በማካሄድ ፣ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂያዊ እዉቀትን በማመንጨት ፣በመቅሰምና በማሰራጨት የህብረተሰቡን ጤና ማሻሻል ፣የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን ቅኝት በማካሄድ እና ስጋቶች ተለይተው ሊደርስ የሚችለውን አደጋ በተገቢው ሁኔታ መከላከል ሲከሰትም ፈጣን እና ብቁ ምላሽ በመስጠት በፍጥነት እንዲያገግም ይደረጋል ብለዋል።
እንደ አቶ ማሙሽ ገለፃ ላቦራቶሪዎች በሰለጠነ የሰው ሀይልና በከፍተኛ ቴክኖሎጂ ማጠናከር ፣ችግር ፈቺ ምርምሮችን ማካሄድ ፣ለህብረተሰቡ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ዉጤታማ ምላሽ የመስጠት ፣አላማን ይዞ የተቋቋመ ተቋም ነው ብለዋል።
ጥሪ የተደረገላቸው የወራቤ ዪኒቨርሲቲ ምሁራኖች፣ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ፣ የቢሮው ማኔጅመንት አባላት እንዲሁም ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈው ይህ የጥናትና ምርምር ጉባኤ እንደቀጠለ ይገኛል ፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያዊ ክልል ጤና ቢሮ