መከላከል በምንችላቸው ምክንያቶች የሚከሰቱ የእናቶችና የህፃናትን ሞት ለመግታት ቅንጅታዊ አሰራር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
እንደ ሀገር የእናቶችና ህፃናትን ሞት በመቀነስ ረገድ በተሰሩ ቅንጅታዊ ስራዎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸው የሚታወቅ ቢሆንም ዛሬም መከላከል በምንችላቸው ምክንያቶች የእናቶችና ህፃናት ሞት እንደሚከሰት በዛሬው ዕለት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የእናቶችና የህፃናትን የሞት መንስኤ እንዲያጠኑ በተለያዩ ሆስፒታሎች ባሰማራቸው የዘርፉ ባለሙያዎች የቀረቡ ግኝቶች ላይ በመከረበት ወቅት ተጠቁሟል።
የዳሰሳ መረጃው በክልሉ በሚገኙ አምስት ሆስፒታሎች ላይ የተደረገ ሲሆን በእናቶችና ጨቅላ ህፃናት ሞት ቅኝትና ምላሽ ላይ እንደ መነሻ የሚሆን ነው፡፡ በወሊድ ምክንያት በተቋማት እና በማህበረሰብ ደረጃ ህይወታቸውን የሚያጡ እናቶችና ጨቅላ ሕፃናት ለሞታቸው ምክንያት የሚሆኑ ችግሮችን መለየትና ዳግም በተመሳሳይ ሁኔታ ሞቶች እንዳይከሰቱ ማድረግ ዋና አላማው ነው፡፡
ለእናቶችና ጨቅላ ህፃናት ሞት ትልቁን ድርሻ የሚይይዙትን ሶስቱ መዘግየቶችን መለየትና ለመዘግየቶቹ ምክኒያቶችን መለየት፤ ለተለዩ ችግሮች ምን መደረግ እንደሚገባውና የጤናውን ስርዓት ማጠናከር የዳሰሳው ዋና አላማ እንደነበርም ተገልጿል ፡፡
በዳሰሳው እንደተመለከተው ለእናቶች ሞት ከሚያጋልጡ ዋና ዋና ምክኒያቶች ውስጥ የደም መፍሰስ፤ ኢንፌክሽን፤ ከእርግዝና ጋር ተያያዞ የሚመጣ የደም ግፊትና የተራዘመ ምጥ ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ ለጨቅላ ህፃናት ደግሞ በዋናነት የመወለጃ ጊዜያቸው ሳይደርስ የሚወለዱ፤ ኢንፌክሽን፤ ሲወለዱ የመታፈን ችግር ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ እናቶቹ ወደ ሆስፒታል ሲመጡም በህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ ተንገላተው መምጣታቸው፤ በሆስፒታሎች የደም አቅርቦት እጥረት ለሞቶቹ የራሱ ድርሻ ያለው እንደሆነም መረጃውን ባቀረቡት ባለሙያ በወ/ሮ ወይንሸት እምሩ ተጠቁሟል፡፡
የማዕከላዊ ኢት/ክ/ህ/ጤ/ኢ/ ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን እና የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትልና የጤና ፕሮግራሞች ዘርፍ ሀላፊ አቶ አሸናፊ ጴጥሮስ ውይይቱን በመሩበት ወቅት ካነሱት አበይት ሀሳቦች ውስጥ የጤና ተቋማት የእናቶች ሞት ኦዲት የሚያደርግ ቡድን አዋቅረው በእርግዝና እና በወሊድ ሳቢያ በእናቶች ላይ የሚከሰት ሞት ላይ ክትትል የሚያደርግና የቅኝትና የዳሰሳ ሥራዎችን የሚሰራ አካል ፈጥረው በመስራት ረገድ ክፍተቶች የተስተዋሉ መሆኑን፣ አብዛኞቹ በወሊድ ምክንያት የሚሞቱ እናቶች ለሞት የሚዳረጉት ከወሊድ በኋላ በሚያጋጥም የደም መፍሰስ በመሆኑ የደም አቅርቦት ላይ አጠናክሮ መሥራት ፣ ከእርግዝና ጋር የተያያዙ ችግሮች ሲከሰቱ ቶሎ በመለየት ተገቢውን የጤና ክብካቤ በወቅቱ ማድረግና ሪፈር ማድረግ ሲያስፈልግ ቶሎ መወሰን እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
በዘርፋ ከፍተኛ ባለሙያዎች በእናቶች ሞት ኦዲት ላይ የተሠራው ሥራ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን እና ችግሩን በመለየት ተገቢውን እርምጃ ለመወሰን ያስችላል ያሉት አስተያየት ሰጪዎች በተለይም የጤና ተቋማት የቅብብሎሽ ሥርዓትንና የተግባቦት አግባባቸውን ማጠናከር ትኩረት የሚሰጠው ተግባር ሊሆን እንደሚገባ በአፅንኦት ተናግረዋል።
ለእናቶች ሞት መንስኤ በመሆን ከተጠቀሱት ችግሮች መካከል ከወሊድ በኋላ በሚከሰት የደም መፍሰስ፤ ከእርግዝና ጋር ተያይዞ በሚከሰት የደም ግፊት፤ በኢንፌክሽን፤ በረጅም ምጥ፣ በደም ማነስ ምክንያትእንደሆነ በመድረኩ የተነሳ ሲሆን እነዚህን ምክንያቶች ማስቀረትና መከላከል የሁሉም የጋራ ኃላፊነት በመሆኑ ቅንጅታዊ አሰራሮችን አጠናክሮ መቀጠል ይገባልም ብለዋል፡፡