የኩፍኝ ወረርሽን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል ስልጠና መሠጠቱ ተገለጸ።
የማዕከላዊ ኢትዮጽያ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከUSAID Quality Health Care Activity ጋር በመተባበር በኩፍኝ ወረርሽኝ ቅኝት(surveillance) እና ህክምና አሠጣጥ(Case management )በተመለከተ በተከታታይ ለሁለት ዙር የቆየው ስልጠና መጠናቀቁን አስመልክቶ ከሰልጣኞች ጋር ውይይት ያደረጉት የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሕብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወልደሰንበት ሸዋለም የኩፍኝ በሽታን ለመቀነስ ሀገራችን በ2001እአአ መደበኛ ክትባትን ከማጠናከር ጀምሮ ደጋፊ የክትባት አገልግሎት (supplemental Immunization Activities), ህክምናና በሽታውን መሠረት ያደረገ አሰሳና ቅኝት እንዲሁም ሌሎች ስትራቴጂዎች ቀርጻ እየተገበረች የቆየች ቢሆንም እንደሀገር በሽታው በወረርሽኝ መልክ እየተከሰተ በመሆኑ አሳሳቢ መሆኑ አውስተው በክልላችንም የማሕበረሰቡ የጤና ችግር ስለሆነ በሽታው ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ሰልጣኞች ከስልጠናው መልስ አገልግሎት በሚሰጡበት አካባቢ ሃላፊነታቸው እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
በተጨማሪም የክትባቶች የቅዝቃዜ ሰንሰለት በማጠናከር ጥራቱን መጠበቅ እንደሚያስችል ገልጸው የተደራሽነት ችግሮች በቁርጠኝነት መፍታት እንደሚያስፈልግና የበሽታው ቅኝትና አሰሳ እንዲሁም የህክምና ስራው በጤና ተቋማት አገልግሎት መስጫ ክፍሎች ከማጠናከር ባሻገር ከጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ጋር ማቀናጀት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ስልጠናው በኩፍኝ በሽታ አሰሳና ቅኝት , በወረርሽኝ ዝግጁነትና ምላሽ ,ህክምና አሰጣጥ , የአደጋ ጊዜ ተግባቦት ግንኙነትና የማሕበሰብ ተሳትፎ እንዲሁም አመራርና ትብብር ላይ ትኩረት ተደርጎ የተሰጠ ሲሆን በሁለቱም ዙር ፕሮጀክቱ ከሚደግፋቸው ወረዳዎች የጤና ድንገተኛ አደጋዎች ስራ ክፍል አስተባባሪዎች እና ከጤና ተቋማት የተውጣጡ አንድ መቶ የሚሆኑ አካላት ተሳትፈውበታል፡፡
ዘገባው ” የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ነው “