በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በወረርሽኝ መልክ የሚነሱ በሽታዎች ቅኝትና ምላሽ አሰጣጥ ስራዎችን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ በዛሬው ዕለት በተደረገው ሳምንታዊ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የድንገተኛ አደጋዎች ኦፕሬሽን ማዕከል (EOC) ተገልጿል ፡፡
ውይይቱን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ሽመልስ ዋንጎሮ እና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በጋራ የመሩት ሲሆን ዋና ዋና የትኩረት መስኮች ሆነው ከተገመገሙ የጤና ጉዳዮች ውስጥ የወባ በሽታ ስርጭት ሁኔታ፣ የምግብ እጥረት፣ ኩፍኝ፣የተቅማጥ በሽታ፣የኤች አይ ቪ ስርጭት ፣የእከክ እና የኮሌራ ስርጭት ያለበትን ደረጃ በመገምገም ሌሎች ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ የታዩ የአፈፃፀም ጉድለቶች ላይ አቅጣጫ ተቀምጧል ።
ከወባ በሽታ ጋር በተያያዘ ከአንዳንድ መዋቅሮች ከሚላኩ አጠራጣሪ ሪፖርቶች በመነሳት ቢሮው የዘርፉ ባለሙያዎችን በማሰማራት በጤና ተቋማቶች ላይ ፍተሻ ያደረገ ሲሆን የወባ ስርጭት ቢኖርም በወረርሽኝ ደረጃ አለመሆኑን ማጥራት እንደተቻለ ተገልጿል፡፡
የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ አቶ ሽመልስ በክልሉ በወረርሽኝ መልክ የተከሰቱ በሽታዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጠንካራ የአሰሳና የቅኝት ሥራዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ በአፅንዖት በመናገር ከግብአት አቅርቦት፣ስርጭት እና አስተዳደር ጋር የሚነሱ ችግሮች በአብዛኛው ከስርቆትና ማጭበርበር ጋር የተያያዙ በመሆናቸው የቢሮው የሚመለከታቸው ክፍሎች ተቀናጅተው ችግሩን በዘላቂነት እንዲፈቱ አሳስበዋል፡፡
የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው የክልሉ የድንገተኛ አደጋዎች ኦፕሬሽን ማዕከል (EOC) በየሳምንቱ የሚያደርገውን የአፈፃፀም ግምገማ ማጠናከር የበሽታዎች አሠሳና የቅኝት ሥራዎችን ይበልጥ በማሻሻል በወረርሽኝ መልክ የተከሠቱ በሽታዎችን ለመቆጣጠር ያስችላል ሲሉ ተናግረው ከየ ዘርፉና ዳይሬክቶሬቱ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል ።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ