በዞኑ ሥር ባሉት ወረዳዎች ለሚገኙ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በክላስተር ደረጃ በሺንሽቾና በዳምቦያ ከተማ የተሰጠው ስልጠና የወባ በሽታ ቅኝትና አሰሳ ስራ በዕዉቀት ላይ ተመስርቶ በመስራትና ለማህበረሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ሁሉንም ማህበረሰብ ክፍሎች ከበሽታው ለመከላከልና እንዲሁም የማህበረሰብ ንቅናቄዎችን ለማጠናከር አጋዥ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የከምባታ ዞን ጤና መምሪያ የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ወጋየሁ ወርቅነህ ሥልናዉን አስመልክቶ እንደተናገሩት የተሰጠዉ ሥልጠና የወባ በሽታን ለመከላከል ጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞችን ተሳትፎ ለማጠናከር፣ የአጎበር አጠቃቀም ለማሻሻል፣ የወባ ትንኝ መራቢያ ቦታዎችን ለማጥፋት ፣ የአካባቢ ቁጥጥር ስራ ለማጠናከር ፣ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን የማፋሰስ ስራ ለመስራት ፣ የወባ በሽታ ምልክቶችን በጥንቃቄ ለይቶ ለማወቅ ምልክቱ የታየባቸው ሰዎች በምርመራ በማረጋገጥ ቶሎ ወደ ጤና ተቋማት ሄደው ህክምና እንዲያገኙ ለማድረግ እንዲቻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለዉ አስገንዝበዋል።
አቶ ወጋየሁ አክለዉም ሥልናዉ በሁሉም መዋቅሮች በሚገኙ ቀበሌያት በሽታው እንዳይከሰትና በሰው ልጅ ሕይወት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳይፈጥር ብሎም በሽታውን ለማጥፋት ህብረተሰቡና ባለድርሻ አካላትን ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ ገልጸዋል።
የከምባታ ዞን ጤና መምሪያ