
የከምባታ ዞን የድንገተኛ አደጋዎችና ወረርሽኞች መከላከልና ቁጥጥር ግብረሀይል የወባ መከላከልና መቆጣጠር ስራን አስመልክቶ በየደረጃው እየተሠሩ ያሉ ተግባራትን የሚገመግም መድረክ በዱራሜ ከተማ አካሂዷል።
በመድረኩም የክረምት ወቅትን ተከትሎ ለወባ ትንኝ መራባት አመቺ የአየር ንብረት ሁኔታ በስፍት የሚታይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን የወባ በሽታ ጫናን ለመግታት በወባ መከላከል፣ መቆጣጠር እና ማስወገድ ዙሪያ በዞኑ በሚገኙ መዋቅሮች እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራት አፈጻጸም እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ዙሪያ የተዘጋጁ ሰነዶች በዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ በዶ/ር ራመቶ አቦ አማካይነት ቀርቦ ሰፊ ዉያይትና ግምገማ ተደርጓል።
በዉይይቱም የወባ በሽታን ለማስወገድ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን ከመተግበር፣ የወባ ሥርጭት በጨመረባቸዉ አካባቢዎች የወባ በሽታ ቅኝትና ምላሽ ተግባራትን ከማጠናከር አንጻር፣ የወባ መራቢያ ቦታዎች ለይቶ የቁጥጥር ስራን ማህበረሰቡን ከማስተባበር አኳያ፣ በጤና ተቋማት የወባ በሽታ ምርመራና ህክምና አገልግሎቱን ከማጠናከርና ከህክምና ግብአቶች አቅርቦት ዙሪያ እንዲሁም በየመዋቅሮቹ የድንገተኛ አደጋዎችና ወረርሽኞች መከላከልና ቁጥጥር ግብረሀይል ከማጠናከር ጋር ተያይዞ በየደረጃዉ የሚስተዋሉ ችግሮች በአፋጣኝ መታረም እንደሚገባቸውም በአፅንኦት ተነስቷል።
መድረኩን የመሩት የከምባታ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊና ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ተክሌ ስዩም የወባ በሽታ ቅኝትና ምላሽ ተግባራትን ማጠናከር ፣የክረምት ዝናብ ተከትሎ ወኃ ያቆሩና ለወባ አስተላለፊ ትንኞች ምቹ መራቢያ ቦታ ስለሚፈጥር በወባ መከላከል ዙሪያ የማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግና የቁጥጥሩ አካል በማድረግ ውኃ ያቆሩ ቦታዎች ማፋሳስና ማደፋን እንደሚገባ፣ የወባ በሽታ ምርመራ እና ህክምና ግብአቶችን በሁሉም ጤና ተቋማት ተደራሽ ማድረግ፣የወባ መከላከልና ቁጥጥር ሥራዎችን በየደረጃው ተቀናጅቶ በመተግበር በሽታዉ የህብረተሰቡን ጤና ስጋት እንዳይሆን ማድረግ የቀጥይ የትኩረት አቅጣጫ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመጨረሻም በወባ መከላከል፣ መቆጣጠርና ማስወገድ ዙሪያ በቀጣይ የሚከናወኑ ተግባራት የድርጊት መርሃ ግብር ዙሪያ የጋራ መግባባት በመፍጠርና አቅጣጫ በማስቀመጥ ዉይይቱ ተጠናቋል።
በግብረሀይል መድረኩ የከምባታ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሾመ ሄራሞ፣የከምባታ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊና ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ተክሌ ስዩምን ጨምሮ የዞኑ የድንገተኛ አደጋዎች እና ወረርሽኞች መከላከልና ቁጥጥር ግብረሀይል አባል ሴክተር መ/ቤት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

