
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ሳምንታዊ ድንገተኛ የህረተሰብ ጤና አደጋዎች አፈጻጸም ውይይት በዛሬው ዕለት ተደርጓል።
የክልሉ ህብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን ድንገተኛ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎችን በተሻለ መንገድ ለመቋቋም የጤና ስርዓቱን ዝግጁነት ለማጠንከር እና መሰረታዊ የጤና አገልግሎቶችን በህብረተሰብ ጤና አደጋዎች ጊዜ ለመስጠት እንዲያስችል የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የተለያዩ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች በሚከሰቱ ሰዓት በቀላሉ መቆጣጠር የሚያስችል የጤና ስርዓት መገንባት አስፈለጊ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ የቅድመ ዝግጅትና የጥንቃቄ ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ከህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አድጋዎች በፊት መደረግ ስላለባቸው የዝግጅት ጉዳዮች፣የህብረተሰብ ጤና አደጋዎችን የመለየት ሂደት፣በማህብረሰቡ ዘንድ ከሚከሰቱ የጤና አደጋዎች በፊት መደረግ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች፣በህብረተሰብ ጤና ድንገተኛ አደጋ ወቅት ስለሚሰሩ ስራዎች እንዲሁም የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች ከተከሰቱ በኋላ ስለሚደረጉ የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባራት በስፋት እና በጥልቀት በመፈተሸ የጤና ስርዓቱን እያጎለበቱ ማስቀጠል እንደሚገባም አቶ ማሙሽ አክለዋል።
የአየር ንብረት ለውጦችን ተከትሎ የወባ በሽታ ጫና እንዳይጨምር የቅድመ ዝግጅት እና የመከላከል እንዲሁም የመቆጣጠር ስራዎችን በቅንጅት መተግበር ይገባልም ነው ያሉት አቶ ማሙሽ።
የወባ በሽታ ጫናን ለመቀነስ የሚያስችል የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባራትን ማጠናከር እንደሚገባ ተመላክቷል።
ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር የወባ በሽታ ጫና እየቀነሰ መምጣቱ የተገለጸ ሲሆን በቀጣይ የአጎበር አጠቃቀም እና የወባ በሽታ መከላከያ ኬሚካል ርጭት ስራን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተጠቁሟል።
በሳምንቱ አፈጻጸም ሪፖርት ትኩረት ይሻሉ ተብለው በተለዩ ጉዳዮች ላይ የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች አጽንኦት ሰጥተው በመምከር የቀጣይ አቅጣጫዎችንም አመላክተዋል።
በዝናሽ ደለለኝ



