Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

በነሀሴ ወር በረዶ የቀላቀለና ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ ዝናብ እንደሚኖር ተመላከተ::

በነሀሴ ወር በረዶ የቀላቀለና ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር የኢትዮጵያ ሜቲዎሮሎጂ ኢኒስቲትዩት አስታወቀ።

ኢኒስቲትዩቱ እ.ኤ.አ ከኦገስት 1 እስከ 31/2025 የሚኖረውን የአየር ጠባይ አዝማሚያ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በነሃሴ ወር ከሚጠናከሩት ዝናብ ሰጭ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ጋር ተያይዞ በተለይም በሰሜን ምስራቅ፣ በሰሜን፣ በመካከለኛዉ፣ በደቡብ ምዕራብና በምዕራብ የሃገሪቱ ቦታዎች ላይ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ተጠቁሟል።

በተጨማሪም በፀሐይ ሀይል ታግዘዉ ከሚፈጠሩ የደመና ክምችቶች በመነሳትም በረዶ የቀላቀለ እና ቅጽበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ መጠን ያለዉ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ተመላክቷል።

እንደ ኢፕድ ዘገባ በሌላ በኩል በአንዳንድ ቦታዎች ከሚኖረው ተደጋጋሚ የሆነ የእርጥበት መብዛት ጋር ተያይዞ በረባዳማ አካባቢዎች የውሃ በሰብል ላይ መተኛት፣ የመሬት አቀማመጡ ከፍታ ባላቸውና ተዳፋታማ በሆኑ አካባቢዎች ደግሞ የመሬት መንሸራተትና በጎርፍ መጠቃት ሊያጋጥም እንደሚችል ተገልጿል።

እንዲሁም እርጥበት በሚበዛባቸው አካባቢዎች የሰብል በሽታ እና የአረም መስፋፋት ሊከሰት ስለሚችል አርሶ አደሮችና የሚመለከታቸው አካላት ሰብሎች በጎርፍ እንዳይጠቁ እና በማሳ ላይ ውሃ እንዳይተኛ የጎርፍ መቀልበሻዎችንና ከማሳ ውሰጥ ውሃን ማንጣፈፊያ ቦዮችን ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል።

የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ ተፋሰሶች ላይ ደግሞ አልፎ አልፎ በሚኖረው ተደጋጋሚ ከባድ ዝናብ ቅጽበታዊ ጎርፍ የማስከተል እድል ይኖረዋል ተብሏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *