Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

ውል የተገባለት የመድኃኒት ፍላጎት እና አቅርቦት ሥርዓት አተገባበር ውጤታማ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት አለባቸው

ውል የተገባለት የመድኃኒት ፍላጎት እና አቅርቦት ሥርዓት አተገባበር ውጤታማ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት አለባቸው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 21/2017(ኢዜአ)፦ ውል የተገባለት የመድኃኒት ፍላጎት እና አቅርቦት ሥርዓት አተገባበር ውጤታማ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ በባህል እና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ታደለ ቡረቃ(ዶ/ር) አስገነዘቡ።

ውል የተገባለት የመድኃኒት ፍላጎት እና አቅርቦት ሥርዓት አተገባበር ሀገር አቀፍ የንቅናቄ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የጤና ሚኒስቴር ከክልሎች ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ጋር በመሆን የህክምና ግብዓት አቅርቦትን መደገፍ፣ የፋይናንስ ምደባና አጠቃቀም ማሻሻል፣ የባለድርሻ አካላትን ትብብር ማጠናከር፣ በማስረጃ የተደገፈ ውሳኔ አሰጣጥ ማጎልበት እና ፍታሃዊና ሁሉ አካታችነት ማረጋገጥ ላይ በትብብር ለመስራት ስምምነት ተፈራርሟል።

በመድረኩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ የባህል እና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ታደለ ቡራቃ(ዶ/ር)፣ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ እና የየክልሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የጤና ቢሮ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ታደለ ቡራቃ(ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ ሚኒስቴሩ የጤናው ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥን ለማቀላጠፍ እያከናወነ ያለው ተግባር አበረታች ነው።

በዚህም የህክምና ግብዓቶች ችግር ለማቃለል እያከናወነ ያለው የአሰራር ማሻሻያ አበረታችና መጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል።

በተለይ በመድኃኒት አቅርቦት ላይ የሚስተዋለውን የማህበረሰብ ቅሬታ ለመፍታት የተጀመረው ውል የተገባለት የመድኃኒት ፍላጎት እና አቅርቦት ሥርዓት ማጠናከር አስፈላጊነትን አብራርተዋል።

ይህ ስርዓት በጤና ተቋማት ያለውን የመድኃኒት አቅርቦት እና ፍላጎት ለማቃለል ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመው ሥርዓቱ የታለመውን ውጤት እንዲያመጣ ክልሎች በቅንጅት መስራት አለባቸው ብለዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ዓመታት ያስቆጠረ የጤና እና የመድኃኒት ፖሊሲ ካላቸው ሀገራት ግንባር ቀደም ናት ብለዋል።

በዚህም አጠቃላይ የህክምና ግብዓት አቅርቦት ስርዓትን ለማሻሻል ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰራ እንዳለም አስረድተዋል።

ውል የተገባለት የመድኃኒት ፍላጎት እና አቅርቦት ሥርዓት አተገባበርን ውጤታማ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብርና ድጋፍ በማድረግ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ፤ የሥርዓቱ አተገባበር በአቅርቦት ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት አይተኬ ሚና አለው ነው ያሉት።

በዚህም ክልሎች አቅርቦት ላይ ችግር እንዳይገጥማቸው ወቅቱ በጀት የሚያዝበት መሆኑን ጠቁመው፤ ለመድሃኒትና ለህክምና ግብዓት በቂ በጀት መያዝ እንዳሚገባ ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *