Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

በጉራጌ ዞን የተቀናጀ የኩፍኝ መከላከያ ክትባትና የጤና ዘመቻ ማስጀመሪያ ፕሮግራም በአበሽጌ ወረዳ ጤና ገራባ ጤና ኬላ ተጀመረ።

በጉራጌ ዞን የተቀናጀ የኩፍኝ መከላከያ ክትባትና የጤና ዘመቻ ማስጀመሪያ ፕሮግራም በአበሽጌ ወረዳ ጤና ገራባ ጤና ኬላ ተጀመረ።

ከግንቦት 6 እስከ 15/2017 በሚካሄደው ዞን አቀፍ የኩፍኝ ክትባት ዘመቻ 193 ሺህ 876 ህፃናት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን የክትባት ፕሮግራሙ ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት የኩፍኝ በሽታ ህፃናትን ለአካል ጉዳትና ለህልፈት የሚዳርግ ተላላፊ በሽታ ሲሆን የማየትና የመስማት ችግር እንዲሁም የሳንባ ምች ያስከትላል ብለዋል፡፡

በሽታ የሚከሰተው ህፃናት መደበኛ ክትባት ባለመከተባቸውና ጥራቱን የጠበቀ የክትባት አገልግሎት ባለመሰጠቱ ህፃናት ለኩፍኝ በሽታ ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸው ገልፀዋል፡፡

የምግብ እጥረት ችግር ያለባቸው ህፃናት፣ ፀጉራቸው የቀላና የሳሳ ሰውነት ያላቸው ህፃናት በኩፍኝ ሲያዙ ለህልፈት የመዳረግ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም እናቶች እድሜያቸው ከ9 እስከ 59 ወር የሆናቸው ህፃናት በሙሉ በዘመቻ መልክ የሚሰጠው የኩፍኝ መከላከያ ክትባት በማስከተብ የልጆቻቸው ጤና መጠበቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ አየለ ፈቀደ እንደገለፁት በተቀናጀ ክትባት ዘመቻው የኩፍኝ ክትባት ፣ ሌሎች የመደበኛ ክትባቶች ያልጀመሩና ያቋረጡ፣ የምግብ እጥረት ያለባቸው ህፃናት ልየታ፣ የቫይታሚን ኤ ጠብታ የመስጠት እንዲሁም ፣የፌስቱላ እና የማህጸን ውልቃት ችግር ያለባቸው እናቶች እና ቆልማማ እግር ያላቸው ህፃናት በመለየት ህክምና እንዲያገኙ የሚደረግበት፣ የታመሙ ህጻናትን የመለየት፣ የአንጀት ትላትል መድሃኒት እደላና ህክምና የሚሰጥበት መሆኑን ተናግረዋል።

በዞን አቀፍ የኩፍኝ ክትባት ዘመቻ 193 ሺህ 876 ህፃናት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የገለፁት ኃላፊው ክትባቱ ቤት ለቤት በመንቀሳቀስና በተመረጡ ማዕከላት የሚሰጥ መሆኑ ተናግረዋል።

ክትባቱ እስከ 10 ቀናት የሚቆይ በመሆኑ እናቶች ሳይዘናጉ ልጆቻቸው ማስከተብ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡

አክለውም ኃላፊው በ2016 በአበሽጌ ወረዳ 72 ህፃናት እና በ2017 በእኖር ኤነር መገር ወረዳ 17 ህፃናት በኩፍኝ በሽታ መጠቃታቸው የተናገሩት ኃላፊው በሽታው በዙሪያ የሚገኝ በመሆኑ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም እናቶች ከግንቦት 06 እስከ 15/2017 በሚሰጠው የተቀናከ ክትባት ልጆቻቸውን ማስከተብ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በተቀናጀ የጤና ዘመቻ እድሜያቸው ከ24 እስከ 59 የሆናቸው 141 ሺህ 635 ህፃናት የፀረ አንጀት ጥገኛ ትላትል መከላከያ ይሰጣቸዋል ብለዋል።

ሁሉም አጥቢና ነፍሰጡር እናቶች የምግብ እጥረት ልየታ እንደሚሰራላቸው አስረድተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *