
(ሆሳዕና፦ሚያዝያ 24/2017)፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት የጤናና ጤና ነክ ድንገተኛ አደጋዎች ቅኝት ምላሽ ዳይሬክቶሬት የ2017 የ9 ወራት አፈጻጸም ግምገማና የህብረተሰብ ድንገተኛ ጤና አደጋዎች ቅኝት እና በመረጃ ስርዓት አተገባበር ዙሪያ የውይይት መድረክ በዱራሜ ከተማ ተካሂዷል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን እንደገለፁት የክልሉ ጤና ኢኒስቲትዩት በህብረተሰቡ ጤና አጠባበቅ ላይ በርካታ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ለኢኒስቲትዩቱ በዋናነት ከተሰጣቸው ኃላፊነቶች መካከል ወረርሽን መከላከል፣ ጥራቱን የጠበቀ የላቦራቶሪ አገልግሎት በክልሉ እንዲኖር ማድረግ፣የጤና ምርምሮችን ማካሄድ እና የጤና መረጃ ቅመራና ትንተና ማዕከላትን ማደራጀት
የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።
በክልል ባለፉት 9 ወራት የኩፍኝ፣ የኮሌራ እና የወባ ወረርሽኝን በመከላከል እና በመቆጣጠር ክልሉ ውጤታ እንደነበረ ገልፀው በቀጣይም ወረርሽኞች ከመከሰታቸው በፊት የቁጥጥር ስራን ማጠናከር ይገባል ነው ያሉት።
የወረርሽኝ ቁጥጥርና አስተዳደር ስርዓትን ማጠናከር፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያና የቅኝት ስራን ማጠናከር፣ፈጣን ምላሽ መስጠት፣ የቅንጅትና የትብብር ስራን ማጎልበት፣ የመረጃን ልውውጥን በቴክኖሎጂ መጠቀም እንደሚገባ ነው አቶ ማሙሽ የገለፁት።
በቀጣይ በዳይሬክቶሬቱ የታዩ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል ደከማ አፈጻጸሞችን በቀሩት ወራት በማረም ለህብረተሰቡ ተገቢውን የጤና አገልግሎትን ለመስጠት መትጋት ያስፈልጋል ብለዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ የሕብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ለገሰ ጴጥሮስ በበኩላቸው ለወረርሽኝ የማይበገር የተቋም ግንባታን በማጠናከር ብሎም ወረርሽኙ ሲከሰት ለመከላከል በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል።
ከዝናብ መምጣት ጋር ተያይዞ በወባ በሽታ ህብረተሰቡ እንዳይጠቃ በጊዜ በወባ ላይ ዘመቻ ማካሄድ ያስፈልጋል ብለው የሪፖርትንና የመረጃ አያያዝ ልውውጥን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች እንደተናገሩት ባለፉት 9 ወራት የወረርሽኝ በሽታዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር እንዲሁም ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመስጠት ረገድ በርካታ ስራዎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራታቸውን ገልፀዋል።
በቀጣይም በዘርፉ የታዩ ውስንነቶችን በማረም በወረርሽኝና በሌሎች በሽታ ምክንያቶች ህብረተሰብ እንዳይጎዳ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
በመድረኩም የዞን፣ልዩ ወረዳ፣የወረዳና ከተማ አስተዳደር እንዲሁም የሆስፒታሎች የPHEM ባለሙያዎችና አስተባባሪዎች ብሎም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
በአድነው አሰፋ







