
(ሆሳዕና፣ሚያዚያ 23/2017)በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በየፓርቲና በመንግስት በዘጠኝ ወራት የተከናወኑ ተግባራት አስመልክቶ ክልል አቀፍ የአመራር መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) እንደገለጹት ፈተናዎቻችንን በመገንዘብ ለተሻለ ለውጥ መስራት ይገባል ብለዋል።
ጥንካሬን ማስቀጠል እና ጉድለትን መለየት እቅድን ለማሳካት የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።
በእቅድ ዝግጅት ወቅት ልዩ ትኩረት በመሰጠቱ አሁን ለተገኘው ውጤት በምክንያትነት ተጠቃሽ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቁመዋል።
የአመቱን ግብ ለማሳካት ተግባሩ የተመራበት መንገድ ስኬታማ እንደነበር ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል ውይይት በማካሄድ የጋራ ተግባቦት መፈጠሩን በአብነት ጠቅሰዋል።
በክልሉ በአፈጻጸም ረገድ የተስተዋሉ ውስንነቶችን በተደረገ ድጋፍና ክትትል እልባት መስጠት እንደተቻለም ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቅሰዋል።
ከሰላምና ጸጥታ አንጻር እንቅስቃሴን የማይገድብ ምቹ የስራ ምህዳር መፈጠሩን ጠቁመዋል።
ሰላምን በማስፈን ረገድ ህብረተሰቡ የነበረው ሚና የላቀ እንደነበርም ርዕሰ መስተዳድሩ አስታውሰዋል።
ከግብርና አንጻር ተጨማሪ የምርት ወቅቶችን በመጠቀም መስራት ተችሏል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
በአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እና ስርጭት ላይ ሲስተዋል የነበረውን ችግር ስርዓት ማስያዝ ተችሏል ብለዋል።
በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 13 ቢሊየን ብር መሰብሰብ መቻሉን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ በቀሪ ወራት የአመቱን እቅድ ለማሳካት በልዩ ትኩረት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በመምህራን እና በትምህርት ዓመራሩ ላይ የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።
ህዝቡን በማሳተፍ የትምህርት ግብአት አቅርቦት ለማሻሻል የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር ተገቢ ነው ብለዋል።
የተቀዛቀዘው የጤና አገልግሎት መስመር ይዟል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በዘርፉ የተጀመሩ ስራዎችን ቀጣይነት ማረጋገጥ ተገቢ ስለመሆኑም አመላክተዋል።
በክልሉ የስራ እድል ፈጠራ ሴክተር በእውቀት እና በእቅድ በመመራቱ ለ193ሺ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን ጠቁመዋል።
በንግድ ስርዓቱ ላይ የሚስተዋለውን ህገወጥነት ለመከላከል የተጀመሩ ስራዎች ሊጠናከሩ ይገባል ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር ) እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ ቀሪ ወራት በሁሉም ዘርፍ የተጀመሩ የፓርቲና የመንግስት ስራዎችን በማቀናጀት መስራት ተገቢ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
የአንድ ኢኮኖሚና ማህበረሰብ ለመምባት በላቀ ቁርጠኝነት እንደሚሰራም አብራርተዋል።
የክልሉ መንግስት ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት የሚያስችል እቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መገባቱን ዶ/ር ዲላሞ ጠቁመዋል።
የክልሉን ጸጋዎች መነሻ ያደረገ እቅድ በመዘጋጀቱ ያለፉት ዘጠኝ ወራት ስራዎች ስኬታማ እንደነበሩም ኃላፊው አመላክተዋል።
የአስተሳሰብ እና የተግባር አንድነትን በማጠናከር ለጋራ ተጠቃሚነት ሊሰራ እንደሚገባም ኃላፊው አብራርተዋል።
በክልሉ ዘላቂ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት መልካም ልምድ ያላቸውን አካባቢዎች ተሞክሮ ማስፋት ተገቢ ስለመሆኑም ዶ/ር ዲላሞ አስረድተዋል።
የፓርቲ አባሉ እና አመራሩ የብልጽግናን እሳቤ እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል ሲሉም አብራርተዋል።
ዘላቂ የህዝብ ተሳትፎን በማጎልበት በልማት ስራ ላይ ያላቸውን ሚና እንዲወጡ መስራት ይገባል ያሉት ኃላፊው የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት ረገድ የአመራሩን ቁርጠኝነት ይጠይቃል ሲሉም ጠቁመዋል።
አመራሩ ሙሉ ጊዜውን በህዝብ አገልጋይነት ስራ ላይ በማዋል የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ እውን ለማድረግ በትኩረት መስራት ይኖርበታል ሲሉም አሳስበዋል።
በብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ይሁን አሰፋ በበኩላቸው በአመራሩ ዘንድ የተግባር እና የአስተሳሰብ አንድነት መፈጠሩን ጠቅሰዋል።
መቀናጀት፣መደጋገፍ ፣መደማመጥ እንዲሁም ተልዕኮዎችን በአግባቡ ተፈጻሚ ለማድረግ እየተካሔደ ያለውን ጥረት አቶ ይሁን አብራርተዋል ።ከክልል ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር የመወያያ አጀንዳዎችን መነሻ በማድረግ ለተሻለ ለውጥ ጥረት መደረጉንም ኃላፊው ጠቁመዋል።ሁሉም አመራር ስራዎችን በመገምገም እና በመከታተል ረገድ ያሳየውን ተነሳሽነት አቶ ይሁን አስረድተዋል።
ሲል የክልሉ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ዘግቧል ፡፡


