Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

ለሕብረተሰቡ ስጋት የሆኑ በሽታዎችን ቴክኖሎጂ በመታገዝ መቆጣጠር መቻሉን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም በወራቤ ዩኒቨርስቲ ተገምግሟል።

የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ለገሰ ጴጥሮስ በዚህ ጊዜ እንደተናገሩት ለሕብረተሰቡ ስጋት የሆኑ በሽታዎችን ቴክኖሎጂ በመታገዝ መቆጣጠር መቻሉን አንስተዋል።

የክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የ”PHEM DHS2″ ቀድሞ ተግባራዊ በማድረግ እውቅና ማግኘቱን ነው አቶ ለገሰ የተናገሩት።

በዘጠኝ ወራት ውስጥ የወባ በሽታ ፈትኖ የነበረ ቢሆንም በተቀናጀ የአመራርና ባለሙያዎች ርብርብ ለመቆጣጠር ተችሏል ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ።

በዘጠኝ ወራት የተመዘገቡ ለውጦችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የባለድርሻ አካላት ሚና የጎላ በመሆኑ በትኩረት እንዲሰራ አቶ ለገሰ አሳስበዋል።

በሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሪሴርችና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከክልሉ ጤና ቢሮ እና በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ጋር በመሆን መጠነ ሰፊ ጥናቶችን አካሂዷል።

በዚህም ከፖሊሲና ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር በሴቶች ልማት ህብረት ጋር በመቀናጀት ጥናቶች የተሰሩ ሲሆን ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር ደግሞ በአዕምሮ ጤና ዙሪያ ጥናት ተካሂዷል።

የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩቱ የተከሰቱ ድንገተኛ የጤና አደጋዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የጎንዮሽና ከላይ ወዳ ታች በቅንጅትና በትብብር ሲያከናውን ቆይቷል።

ከክልሉ አደጋ ስጋት አመራር ጋር በመቀናጀት ለምግብ እጥረትና ተያያዥ ድንገተኛ አደጋዎች ተጋላጭ ወረዳዎች የመኸር ዳሰሳ ተከናውኗል።

የኩፍኝ ወረርሽኝን በተመለከተ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ተጠርጣሪ ኬዞች ሪፖርት ተደርገው በላቦራቶሪ መረጋገጣቸው፤ እንደክልል 433 የኩፍኝ ታማሚዎች ሪፖርት የተደረገ ሲሆን ሞት ሳይከሰት መቆጣጠር ተችሏል።

ሐዋሳ የክልል ላቦራቶሪ፤ የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ላቦራቶሪ እና የጂማ ዩኒቨርስቲ ሜዲካል ኮሌጅ ላቦራቶሪ ናሙናዎችን በፖስታ ቤት አማካይነት አሊያም በአማራጭ የናሙና ቅብብሎሽ ሰንሰለትን በመጠቀም ለህሙማን የምርመራ አገልግሎት መስጠት ተችሏል፡፡

የቲቢ ምርመራን በጂን ኤክስፔርት ማሽን በሚመለከት በአጠቃላይ 33,788 ናሙናዎች ለቲቢ በጂን ኤክስፔርት ማሽን ምርመራ ተደርጓል።

በቲቢና በወባ ምርመራ ውጫዊ ጥራት ቁጥጥር በስላይድ መልሶ ምልከታ ከሚሳተፉት ጤና ተቋማት የመልሶ ምልከታ የውጤት ልዩነት ያለባቸውን እንዲሁም በመስፈርቱ መሠረት በመልሶ ምልከታ የማይሳተፉትን ጤና ተቋማት በተቋሙ ስታንደርድ ቼክ ሊስት በመጠቀም የሜንተርሺፕ ቅድሚያ በመስጠት ድጋፋዊ ክትትልና ሜንቴርሽፕ ሥራ ለማከናወን ተችሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *