
30ኛው የሜዲካል ላቦራቶሪ የሙያ ማህበር አመታዊ ሳይንሳዊ ጉባኤና አለማቀፍ የሜዲካል ላቦራቶሪ ባለሙያዎች ሳምንት “ላቦራቶሪ ሕይወት ያድናል!” በሚል መሪ መልዕክት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ በተገኙበት ተከብሯል።
የላቦራቶሪ አገልግሎት በግልና በመንግስት ተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር ፈር ቀዳጅ ልምድ ያለው መሆኑን የጠቀሱት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ የኮቪድ ወረርሽን የላቦራቶሪ አቅማችንን ለማሳደግ መልካም አጋጣሚ ፈጥሮልናል፤ አሁንም በትኩረት እየተሰራ ነው በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የላቦራቶሪ አቅምን ለማሳደግ እየተሰራ ያለዉ ስራ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል። አያይዘውም ከውጭ ስናስመጣ የነበሩ የህክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ደረጃም አበረታች ጅማሮ መኖሩን አብራርተዋል።
70 በመቶ ያህል የህክምና ውሳኔዎች በላቦራቶሪ ላይ የተመሰረቱ መሆናቸውን የገለፁት የሜዲካል ላቦራቶሪ ሙያ ማህበር ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር አስቴር ፀጋየ በበኩላቸው በህክምና ሙያ የህሙማን ደህንነት ቀዳሚ ጉዳይ በመሆኑ የሜዲካል ላቦራቶሪ ጥራት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። የኮቪድ ወረርሽኝ የሜዲካል ላቦራቶሪን አስፈላጊነት በጉልህ ማሳየቱን ያስታወሱት ፕሮፌሰር አስቴር የሙያ ማህበሩ ከመንግስት እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑንና ወደፊትም ይህንኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ጥናታዊ ፅሁፍና ፓናል ውይይቶች ቀርበው ውይይት በተደረገበት አመታዊ መድረክ ጤና ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣንና የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ አገልግሎትን ጨምሮ አስተዋፅኦ ያደረጉ ተቋማት እውቅና ተሰጥቷቸዋል::



