Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

በዞን ደረጃ ሁላቀፍ የጤና ኤክስቴንሽን ተግባራትን በተደራጀ አግባብ በመምራት የዘርፉን አገልግሎት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሻገር ከፍ ባለ ቅንጅት እንዲሰራ ተጠየቀ።

በስልጤ ዞን ደረጃ ሁላቀፍ የጤና ኤክስቴንሽን ተግባራትን በተደራጀ አግባብ በመምራት ጉድለቶችን ለመፍታትና የዘርፉን አገልግሎት ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሻገር ባለድርሻ አካላት ከፍ ባለ ቅንጅት እንዲሰሩ የስልጤ ዞን ጤና መምሪያ ጠይቋል።

መምሪያው የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበትና የዞኑን የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም አፈጻጸም ማሻሻል ላይ ያተኮረ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።

በንቅናቄ መድረኩ ላይ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ትግበራን ለማሻሻል የተዘጋጀ የውይይት ሰነድ በስልጤ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ በአቶ ሸምሱ ሀይረዲን ቀርቦ ምክክር ተደርጓል።

በዞን ደረጃ የጤና ኤክስቴንሽን ከተጀመረበት ከ1997 ጀምሮ 197 በላይ ጤና ኬላዎች በህዝብና መንግስት ትብብር ተገንብተው ወደ ስራ መግባታቸው ሲገለጽ በዚህም ከ400 በላይ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉ በሰነዱ ተመላክቷል።

የጤና ኤክስቴንሽን ትግበራ በሀገርና በዞን ደረጃ በጤናው ዘርፍ ከፍተኛ እምርታ እንዲመዘገብ ማስቻሉ ተገልጾ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እነዚህን እምርታዊ ለውጦች ማስቀጠል ያለመቻል ችግሮች በስፋት መስተዋላቸው ተጠቁሟል።

ችግሩን ከመፍታት አንጻር ሰፋፊ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በማንሳት በተሻሻለው የጤና ፖሊሲ ፕሮግራሙ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት የ7 ዓመታት የጤናው ዘርፍ የልማትና ኢንቨስትመንት እቅድ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱም ነው የተገለጸው።

በተሻሻለው የጤና ፖሊሲ ከጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም አንጻር የጤና ኬላዎች አደረጃጀትና አወቃቀር ላይ ለውጥ ማድረግ፣ በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የሚሰጡ አገልግሎቶችን ፓኬጅ ማስፋፋት፣ የጤና ኬላዎችን አገልግሎት ፓኬጆችና አደረጃጀት መሰረት ያደረገ የሰው ሀይል እና የግብዓት ማሻሻያ ማድረግ እንዲሁም በተዘጋጀው ሀገራዊ ስታንዳርድ መሰረት የጤና ኬላዎችን መሰረት ልማት ማሻሻል የሚሉ ዝርዝር ተግባራት ተቀምጠው እየተሰራ እንዳለም በመድረኩ ቀርቧል።

በመድረኩ ላይ በቀረቡ ዝርዝር ጉዳዮችና ከጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ በዞን ደረጃ ባሉ ጉድለቶች ላይ ሰፊ ምክክር በማድረግ ከመግባባት ተደርሷል።

የውይይት መድረኩን የመሩት የስልጤ ዞን ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ሸረፋ ሌገሶ በዞን ደረጃ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሞችን በተሻሻለው ፖሊሲ መሰረት ለማደራጀትና ተግባሩን በቅንጅት እንዲመራ ለማድረግ በሚሰራው ስራ ውስጥ የዞኑ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

የዞኑ ህዝብ የመንግስትን የልማት እንቅስቃሴዎች በመደገፍ በኩል በርካታ እቅዶችን በማህበረሰብ ተሳትፎ እያሳካ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ሸረፋ ይህን አቅም ተጠቅሞ የተጀመሩ ኮምፕርሄንሲቭ ጤና ኬላዎችን ማጠናቀቅና ሌሎች ተግባራትን ማሳለጥ ይገባል ብለዋል።

ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በሁሉም ቀበሌያት ምቹ የስራ ከባቢን መፍጠር፣ የጤና ኬላ ግብዓት ማሟላትና ሌሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት ላይ መዋቅሮች ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አቶ ሸረፋ አሳስበዋል።

የስልጤ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ ሸምሱ ሀይረዲን የጤና ኤክስቴንሽን የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻልና አዲሱን ፖሊሲ ለመተግበር በመምሪያው በኩል ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።

ንቅናቄው ጅምሮችን በማጠናከር እቅዱን ሙሉ በሙሉ ለማስተግበር እንደሚያግዝ ያነሱት አቶ ሸምሱ መሰል የንቅናቄ መድረኮች በታችኛው መዋቅር እንደሚደረጉ ገልጸዋል።

አሁን ላይ በዞኑ የተለያዩ አከባቢዎች የተጀመሩ አጠቃላይ ጤና ኬላዎች ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ሀላፊው በሌሎች አከባቢዎች አዲሱን ስታንዳርድ መሰረት ያደረጉ ጤና ኬላዎችን ለመገንባት መታቀዱንም አስረድተዋል።

ጤና ኬላዎችን በተሻለ ግብዓት ማደራጀት የሰው ሀይል አደረጃጀቱን ማጠናከርና ማህበረሰባዊ ተሳትፎን ማጎልበት ላይ ከመዋቅሮች ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አቶ ሸምሴ አስታውቀዋል።

በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ የተሻለ ለፈጸሙ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች የማበረታቻ ሽልማት በማበርከት ዝግጅቱ ፍጻሜውን አግኝቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *