Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

ኢትዮጵያ እና ሩሲያ የጤና ትብብርን ለማጠናከር የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

በኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር እና በሩሲያ የሸማቾች መብት ጥበቃ እና የሰብአዊ ደህንነት ክትትል አገልግሎት የመግባቢያ ስምምነቱ ተፈርሟል። ፊርማው የተካሄደው ለመጀመሪያ ጊዜ የሩሲያ-አፍሪካ ለድንገተኛ የጤና አደጋዎች ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድኖች ልምምድ እና አውደ-ጥናት መርሃ-ግብር ጎንዮሽ ሲሆን፤ በጤና ድንገተኛ አደጋዎች ላይ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር ያለመ ስምምነት ነው፡፡

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ኢትዮጵያን ወክለው፣ የሩስያ የሸማቾች መብት ጥበቃ እና የሰብአዊ ደህንነት ክትትል አገልግሎት ኃላፊ አና ፖፖቫ ሀገራቸውን ወክለው ፈርመዋል። ይህ የመግባቢያ ሰነድ ከጤና እና ንፅህና ጋር በተያያዙ ድንገተኛ ሁኔታዎች በተለይም በወረርሽኝ ወይም የጤና አደጋዎች በሚከሰቱበት ጊዜ የሚሰጥን ፈጣን ምላሽን በማሻሻል ላይ ያተኮረ ነው።

በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ዶ/ር መቅደስ ዳባ በጤና ላይ አለም አቀፍ ትብብር ያለውን ጠቀሜታ አጽንኦት ሰጥተዋል። በትብብር መስራት ሀገራት እውቀትና ሃብት እንዲለዋወጡ የሚያስችል መሆኑን ገልጸው፤ ይህም የጤና ድንገተኛ አደጋዎችን በብቃት ለመቆጣጠር ወሳኝ ነው ብለዋል።

አና ፖፖቫ የዚህን ስምምነት አስፈላጊነት በማጉላት ሁለቱም ሀገራት ለድንገተኛ የጤና አደጋዎ በተሻለ ሁኔታ እንዲዘጋጁ እና የዜጎቻቸውን ደህንነት ለመጠበቅ እንደሚረዳ አስረድተዋል። ትብብሩ የእያንዳንዱን ሀገር የጤና ስጋቶች ምላሽ የመስጠት አቅምን ለማሳደግ መረጃን መለዋወጥ፣ ስልጠና እና ምርጥ ተሞክሮዎችን መጋራትን ያካትታል።

ይህ ስምምነት በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል በጤናው ዘርፍ ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ወሳኝ እርምጃ ነው። ሁለቱም ሀገራት የጤና ድንገተኛ ሁኔታዎች ሲገጥሟቸው በፍጥነት እና በብቃት እንዲሰሩ እና በመጨረሻም የህዝብ ጤናን ለህዝቦቻቸው እንዲያሻሽሉ ለማድረግ ያለመ ነው።

የመግባቢያ ሰነዱ በተፈረመበት መድረክ ከ110 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ተንቀሳቃሽ ላብራቶሪ ከነ ሙሉ መሳሪያዎቹ የሩሲያ መንግስት ድጋፍ አድርጓል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *