
አዳዲስ ፈጠራዎችን እና ሀብትን በማቀናጀት በሁሉ አቀፍ ቁርጠኝነት ወባን እንግታ!” በሚል መሪ ቃል በሀገራችን ኢትዮጵያ ለ18ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአለም ወባ ቀንን አስመልክቶ የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ዶ/ር ደረጀ በአገራችን እየጨመረ ያለውን የወባ ስርጭት ለመቀነስ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ገልፀው፣ ወባን ለማጥፋት ዘርፈ ብዙ ምላሽ የሚጠይቅ ስራ እንደሚያስፈልግና ሁሉም ባለድራሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
የሀገራችን መልከዓ ምድር 75 በመቶ የሚሆነው ለወባ በሽታ ስርጭት አመቺ ሲሆን 69 በመቶ የሚሆነው ህዝባችን ለወባ በሽታ ተጋላጭ መሆናቸውን በተለይም የክረምት ዝናብን ተከትሎ ከመስከረም እስከ ታህሳስ ድረስ ባለው በምርት መሰብሰቢያ እና ከበልግ ዝናብ በኋላ ከመጋቢት እስከ ግንቦት ባለው ወቅት የወባ ታማሚ ቁጥር ሊጨምር ስለሚችል ማህበረሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግና ጤና ተቋማትም ተገቢውን የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው ዶክተር ደረጀ አሳስበዋል፡፡
በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከል መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶ/ር ህይወት ሰለሞን የአጎበር ስርጭትና የመድሐኒት አቅርቦትን በተመለከተ ከጋዜጠኞች ለቀረቡ ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ አጎበር ገዝቶ ለማኅበረሰቡ ለማሰራጨት በታቀደው መሰረት 2.2 ሚሊዮን የመኝታ አጎበር እንደተሰራጨ እና የፀረ- ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት በተመረጡ 167 ወረዳዎች ውስጥ የሚገኙ 1.8 ሚሊዮን ቤቶች ቤት ለቤት በመሄድ አገልግሎቱን ማቅረብ እንደተቻለም ተገልጿል፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ ስልታዊ የሆነ የወባ ማጥፋት ስትራቴጂን በመከተል በተለይ ስርጭቱ እየጨመረ ያለባቸው አከባቢዎች ላይ በየደረጃው ያሉ አመራሮችን እስከ ጤና ኤክስቴንሽ ባለሞያዎች በትኩረት እየሰሩ ያሉበትን ሒደት ያስረዱት በጤና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ተገኔ ረጋሳ ናቸው፡፡
ለተከታታይ ሁለት ቀናት አገራዊ ሳይንሳዊ ጉባዔ በኦሮሚያ ክልል በጅማ ከተማ እንደሚካሄድ፣ የተሰሩ የምርምር ስራዎች እንደሚቀርቡ እንዲሁም የማህበረሰቡን ንቅናቄ ለማሻሻል ከባለድርሻ አካላት ጋር ስለሚመክርበት ሁኔታም ተጠቁሟል፡


