Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

በኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ ላይ እየታየ ያለውን መዘናጋት ለማስቀረት ጉዳዩን ቀዳሚ አጀንዳ በማድረግ መስራት እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር )

በኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ ላይ እየታየ ያለውን መዘናጋት ለማስቀረት ጉዳዩን ቀዳሚ አጀንዳ በማድረግ መስራት እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር )

አሳሰቡ

(ሆሳዕና ሚያዚያ 3/2017) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ላይ ያተኮረ የንቅናቄ መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር ) በውይይት መድረኩ ማጠቃለያ በሰጡት የስራ መመሪያ እንዳስታወቁት በኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ ላይ እየታየ ያለውን መዘናጋት ለማስቀረት ጉዳዩን ቀዳሚ አጀንዳ በማድረግ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከዚህ ቀደም ተጋላጭ ከሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በተጨማሪ ሌሎችም ለበሽታው ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች መኖራቸውን ያመላከቱት ርዕሰ መስተዳድሩ ችግሩን ለመቅረፍ መገናኛ ብዙሀን፣የእምነት ተቋማት፣ተጽዕኖ ፈጣሪ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ሌሎችም አካላት በትኩረት መስራት አለባቸው ብለዋል።

ከተቋማት ለኤድስ ፈንድ እየተዋጣ ያለውን ሀብት በተገቢው መንገድ ማስተዳደር ተገቢ ስለመሆኑም ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።

በትምህርት ተቋማት ለተማሪዎች ስለ በሽታው አስከፊነት ማስተማር ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን ግንዛቤ ማስጨበጥ እንደሚገባ የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ ቫይረሱ ለተገኘባቸው ዜጎች ድጋፍና ክብካቤ ያሻል ሲሉም ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል የማህበረሰብ ጤና መድህን ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የአገልግሎት እድሳት እና አዳዲስ አባላትን በማፍራት ረገድ የተጀመሩ ስራዎችን ማጠናከር እንደሚገባም አስረድተዋል።

በዘርፉ ለሚካሄደው ሁሉን አቀፍ ጥረት አጋዥ እንዲሆን ወደ ባንክ ያልገባ ገንዘብ መፈተሽ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ መዋጮ መክፈል የሚገባቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ሚናቸውን እንዲወጡ መስራት ተገቢ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

መክፈል ለማይችሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን በልዩ ሁኔታ መደገፍና የጤና ተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥን ማቀላጠፍ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በህክምና ግብአት አቅርቦት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት አቅዶ መስራት ተገቢ ስለመሆኑም አውስተዋል።

ህብረተሰቡ በማህበረሰብ ጤና መድህን ላይ ያለውን እምነት አስተማማኝ ለማድረግ በዘርፉ የሚሰጠውን አገልግሎት ማዘመን ይገባል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህም የጤና ባለሙያዎች እና አመራሩ በልዩ ትኩረት እንዲሰሩ አሳስበዋል።

የማህበረሰብ መድሀኒት ቤት ግንባታ ውጤታማ በማድረግ ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የክልሉ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ -ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ሰርሞሎ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ስለ በሽታው አስከፊት ይደረግ የነበረው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መቀዛቀዙን ጠቁመዋል።

የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በቁርጠኝነት መስራት ይገባል ያሉት ዋና አፈጉባኤዋ የክልሉ መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ልዩ ትኩረት ማጠናከር ተገቢ ስለመሆኑም አመላክተዋል።

በብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር ) እንደገለጹት የኤች አይቪ ኤድስ በሽታውን ለመከላከል የተጀመረው ጥረት ለሀገር እና ለመጪው ትውልድ መኖር የሚያመላክት ነው ብለዋል።።

ትውልዱ እየተዘናጋ ነው ያሉት ዶ/ር ዲላሞ ከተዘናጋን ደግሞ በሀገር እልውና ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዕኖ ትውልድ እንዳይቀጥል ያደርጋል ብለዋል።

ብልጽግና ፓርቲ በሰው ተኮር ፕሮግራሞቹ ከሚተገብራቸው ስራዎች አንዱ ኤች አይቪ ነው ብለዋል።

የቫይረሱን ስርጭት አጀንዳ አድርጎ መስራት ተገቢ ስለመሆኑም አመላክተዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ እንዳሉት ኤች አይ ቪ ኤድስ በህብረተሰቡ ጤና ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመከላከል በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።

በትምህርት ተቋማት ክበባትን በማቋቋም እየታየ ያለውን መዘናጋት ለማስቀረት የተቀናጀ ጥረት እንደሚጠይቅ አቶ አንተነህ አብራርተዋል።

ተማሪዎች ስለ ቫይረሱ አስከፊነት እንዲገነዘቡ መስራት ይገባል ያሉት ኃላፊው ለዚህም የሁሉንም አካላት ዝግጁነት ይጠይቃል ብለዋል።

የክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ኤርሲኖ አቡሬ በበኩላቸው የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ማጠናከር ይገባል ብለዋል።

በክልሉ በኤች አይ ቪ የመያዝ ምጣኔ እየጨመረ ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ ይህም በህብረተሰቡ ዘንድ መዘናጋት እንዳለ አመላካች ነው ብለዋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር እንደገለጹት የኤች አይቪ ኤድስን ስርጭት ለመግታት ሁሉንም የመገናኛ ብዙሀን አውታሮችን በመጠቀም ህብረተሰቡን ማስገንዘብ ይገባል ብለዋል።

በሽታው በምርታማነት ላይ የተጀመረውን ጥረት አደናቃፊ መሆኑን በመገንዘብ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የጋራ ጥረት ይጠይቃል ሲሉም አቶ ኡስማን አብራርተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *