Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

ከ338 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ህገ-ወጥ የመድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እና ጉምሩክ ኮሚሽን በጋራ በሰጡት መግለጫ ከ338 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጡ ህገ-ወጥ የመድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎች መያዛቸውን ገልጸዋል።

ከህወጥ ድርጊቱ ጋር በተያያዘ 19 ተጠርጣሪ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ስዩም ወልዴ ባለስልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ባለፈው ሳምንት በአዳማና በአዲስ አበባ ከተሞች በ23 ቦታዎች ህገ-ወጥ የመድሃኒት ዝውውር ቁጥጥር ስራ ማከናወኑን ተናግረዋል።

በተደረገው የቁጥጥር ስራ ግምታዊ ዋጋቸው 118 ሚሊየን ብር የሆነ የተለያዩ መድሃኒቶች ተይዘዋል ብለዋል።

ግምታዊ ዋጋቸው 150 ሚሊየን ብር የሆነ ጥቅም ላይ የማይውሉ የህክምና መሳሪያዎች እንዲሁም 70 ሚልየን ብር የሚገመቱ ተገቢው የጥራት ምርመራ ተደርጎባቸው አገልግሎት ላይ የሚውሉ የህክምና መሳሪያዎች እንደሚገኙበት በመግለጫቸው አንስተዋል።

በአጠቃላይ ግምታዊ ዋጋቸው ከ338 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ህገ-ወጥ መድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ነው ያሉት።

ህገ-ወጥ መድኃኒቶች ወደ ገበያ ሲገቡ ጥራታቸው፣ ደህንነታቸውና ፈዋሽነታቸው ባለመረጋገጡ በህብረተሰቡ ላይ የጤና፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳትን እንደሚያስከትሉ ጠቅሰዋል።

የመጠቀሚያ ጊዜ አልፎባቸው እንደ አዲስ የመጠቀሚያ ጊዜ የተለጠፈባቸው መድኃኒቶች፣ በባለስልጣኑ ያልተመዘገቡና የገበያ ፍቃድ የሌላቸው ህገ-ወጥ የጤና ግብዓቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ህገ-ወጥ መድኃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎችን ለመያዝ በተደረገው ጥረት ህብረተሰቡ ላደረገው ትብብር ምስጋና በማቅረብ በቀጣይም የቁጥጥር ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር እዘዘው ጫኔ በበኩላቸው ህገ-ወጥ የመድሃኒት ዝውውርን ለመቆጣጠርና ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከኢንተርፖል እና ከክልል የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በተደረገ ክትትል በህብረተሰቡ ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ህገ-ወጥ መድሃኒቶችና የህክምና ቁሳቁሶች መያዛቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የብሔራዊ ኢንተርፖል ድንበር ዘለል ወንጀሎች እና ኦፕሬሽን ዋና ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ጥሩወርቅ መንግስቴ በበኩላቸው ኢንተርፖል ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል ህገ-ወጥ የምግብና መድሃኒት ዝውውር አንዱ ነው ብለዋል።

በአዲስ አበባ እና በአዳማ በቅንጅት የተሰራው ህገ-ወጥ መድኃኒቶችና የህክምና መሳሪያዎችን የመቆጣጠር ስራ ውጤት ማመጣቱን ጠቅሰው በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስተዋል።

ኢዜአ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *