Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

የኩላሊት ህመምና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ቅድመ ምርመራዎችን ማድረግና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ መከተል ይገባል!

የኩላሊት ህመም ቀንን ምክንያት በማድረግ በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ በጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከል መሪ ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ህይወት ሰለሞን ባስተላለፉት መልዕክት የኩላሊት ህመምን ጨምሮ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሚያስከትሉት ጉዳት እየጨመረ እንደሆነ ጠቁመው ቅድመ ምርመራዎችን በማደረግና ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ በመከተል መከላከል ስለሚቻልበት ሁኔታ አብራርተዋል፡፡

በአገራችን የኩላሊት ህመም አሳሳቢ የህብረተሰብ የጤና ስጋት መሆኑንና ጥቂት የማይባሉ ዜጎች የጉዳቱ ሰለባ እየሆኑ በመምጣታቸው በህክምና ተቋማት የመመርመር አቅምን ለማሳደግ ጤና ሚኒስቴር በትኩረት እየሰራበት እንደሆነ የተናገሩት በሜዲካል አገልግሎት መሪ ስራ አስፈጻሚ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር አብዲ ደረጀ ናቸው፡፡

በጥቁር አንበሳ ስፔሻላዝድ ሆስፒታል የኩላሊት ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር የወንድወሰን ታደሰ የጤና ባለሞያዎች ህመምተኞች ወደ ጤና ተቋማት በሚመጡበት ጊዜ ቢያንስ የሽንት ምርመራ እና የደም ግፊት ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸው ከህክምናው ጎን ለጎን ግንዛቤ በማስጨበጥ ሞያዊ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

የስነ ልቦና ባለሞያ የሆኑት ዶክተር እስጢፋኖስ እንዳለማው በበኩላቸው ስር የሰደደ የኩላሊት ህመም ያለባቸው ሰዎች ለድባቴ ህመም የሚጋለጡበት ሁኔታ ስለሚኖር በሂደት ማህበራዊ ቀውስ የሚያስከትልበት ሁኔታ እንዳይባባስ ከኩላሊት ህክምናው በተጓዳኝ በጤና አገልግሎት መስጫዎች የስነ ልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ መሰራት አለበት ብለዋል፡፡

የኩላሊት ንቅለ ተከላ እና የኩላሊት እጥበት ታካሚዎች በተስፋ የኩላሊት ታማሚዎች ማህበር ተገኝተው በህመሙ ከተያዙ ጊዜ ጀምሮ ያጋጠሟቸውን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውሶች ገልፀው፤ በእኛ ይብቃ ህብረተሰቡ ምንም አይነት መድሃኒት ያለ ሀኪም ትዕዛዝ አይውሰድ፣ አስቀድሞ የመመርመር ባህልን እናዳብር ብለዋል፡፡

“አስቀድመው ይመርመሩ፣ የኩላሊትዎን ጤና ይጠብቁ!” በሚል መሪ ቃል የኩላሊት ቀን መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም ተከብሯል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *