Central Ethiopia,Worabe
cerphi@cerphi.gov.et

የፖሊዮ ክትባት በክልሉ ከፊታችን ዓርብ የካቲት 14-17/2017 ዓ.ም ይሰጣል

(ሆሳዕና:- የካቲት 12/2017) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ከየካቲት 14-17/2017 ዓ/ም የሚካሄደውን ክልል አቀፍ የመጀመሪያው ዙር የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ አስመልክቶ ለመገናኘት ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።መግለጫውን የክልሉ ጤና ቢሮና በቢሮው የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ ሰጥተዋል።

የቢሮው ሀላፊ አቶ ሳሙኤል ዳርጌ በመግለጫቸው በክልሉ ከየካቲት 14-17/2017 ዓ/ም ክልል አቀፍ የመጀመሪያው ዙር የፖሊዮ(የልጅነት ልምሻ) ክትባት ይሰጣል ብለዋል።

የፖሊዮ በሽታ በአገራችን ለብዙ ህጻናት ህመም፣ የአካል ጉዳትና ሞት ምክንያት ከሆኑት በሽታዎች መካከል አንዱ ነዉ ብለዋል።

ክትባቱ እድሜያቸው 5 አመት እና ከ5 በታች ለሆኑ ህፃናት ቤት ለቤት የሚሰጥ ሲሆን በዘመቻው በሁሉም ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ከ1ሚሊዮን 51ሺ በላይ ህፃናትን ለመከተብ መታቀዱን በመግለጫው አስታውቀዋል።

ፖሊዮን ከሀገሪቱ ለማጥፋት በክትባት አያያዝና አሰጣጥ ጥራት ላይ ትኩረት መደረግ አለበት ብለዋል።

ክትባት ያልወሰዱና ያቋረጡ ህጻናት ፣ በምግብ የተጎዱ ህጻናት ልየታ እና የቆልማማ እግር ልየታ የዘመቻው አካል ተደርጎ ይሰራሉ ብለዋል።

የቆልማማ እግርና የከንፈር መሰንጠቅ ችግር በክልሉ በ6 ሆስቲታሎች አገልግሎት እየተሰጠ በመሆኑ ወደ ጤና ተቋማት በማምጣት ህክምና እንዲያገኙ እንዲደረግ አሳስበዋል።

የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህንን ለዜጎች በፍትሃዊነት በክልሉ ተደራሽ ለማድረግ በዘመቻው ህብረተሰቡን የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ሚዲያው ለዜጎች በአካባቢው ቋንቋ መረጃዎችን በወቅቱ ተደራሽ በማድረግ ግንዛቤ የመፍጠር ስራን አጠናክረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

ህፃናት ከዚህ በፊት የፖሊዮ ክትባት ቢከተቡም ባይከተቡም በዘመቻው ይከተባሉ ብለዋል።

በክትባት ወቅት የጎንዮሽ ጉዳት ቢያጋጥም ፈጥኖ መረጃ መስጠት ይገባል ያሉት ሀላፊው ይህንኑ የሚቆጣጠር የክልሉ የጤናና ጤና ነክ ቁጥጥር ቡድን መመደቡን አስታውቀዋል።

ሁሉም ባለድርሻ አካላት ህብረተሰቡን በማስተባበር ፖሊዮን ከሀገራችን ለማጥፋት በሚደረገው ርብርብ በጋራ እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የቢሮው የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን በክልሉ ፀረ ፖሊዮ ክትባት ለሁሉም ህፃናት በመደበኛነት እየተሰጠ ነው ብለዋል።

ክትባቱ በሰውሰራሽና ተፈጥሯዊ ምክንያት ተደራሽ ባልሆኑባቸው አካባቢዎች እና በሀገር አቀፍ ደረጃ በ7 ክልሎች በሽታው ሪፖርት በመደረጉ ምክንያት በዘመቻ መስጠት ማስፈለጉን ተናግረዋል።

ፖሊዮ ማላታይስ በሚባል ተዋህስ (ቫይረስ) የህፃናት ህብለሰረሰር በማጥቃት የሰውነት ሽባነት የሚያስከትል ሲሆን አለፍ ሲልም ሞት የሚያመጣ በሽታ ነው ብለዋል።

በሽታው ከእጅ ወደ አፍ በሚገባ ቫይረስ የሚተላለፍ በመሆኑ ህፃናት በዚህ ዕድሜ ተጋለጫ መሆናቸውን አቶ ማሙሽ ተናግረዋል።

ዘመቻው በመደበኛው ክትባት የሚፈጠረውን ክፍተት ለመሸፈን አጋዥ መሆኑን ተናግረው ህፃናት ቀጣይ የሀገር ተረካቢዎች በመሆናቸው ትኩረት መስጠት ይገባልም ብለዋል።

የቅድመ ዝግጅት ስራው መጠናቀቁን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ በሽታውን በቀላሉ በክትባት መከላከል የሚቻል ስለሆነ ወላጆች ህፃናትን በወቅቱ ማስከተብ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ክትባቱ ለተከታታይ 4 ቀናት የሚሰጥ በመሆኑ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በንቃት መሳተፍ እንዳለባቸው በመግለጫው ተመላክቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *